Tuesday, 9 June 2015

ክብር ለሰማዕታት!


የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ እያለሁ ስለ ደርግ ገዢዎች የሚነዙትን ጭራቅነት አስታውሳለሁ፤ ይህም ደርግ የሚባለው ወታደራዊ አስተዳደር በአይምሮዬ በመጣ ቁጥር የሚሰማኝ እምብዛም መልካም ነገር አልነበረም፡፡ ያው በዚህ ስርዐት ዘመን ተወልጄ አንደማደጌ መጠን የሚነዙት ፕሮፓጋንዳ የፈጠረብኝ ነገር ቀላል አልነበረም፡፡ ትላንት የደርግን ጭራቅነት ሲግቱን የነበሩት ከፋፋይና አምባገነን መሪዎች ዳግማዊ ጭራቅነት ለመረዳት ግን ብዙም አልዘገየሁም፡፡በሁለቱ አምባገነን ስርዐቶች መካከል ያለውን ልዩነት ሳስታውስ ደርግን ጅል አምባገነን ሆኖ አገኘዋለሁ፡፡ አሁን ያሉትን ደግሞ ብልጥ አምባገነን፡፡

ደርግ ምርጫ፣መድብለ ፓርቲ ነፃ ፕሬስ ምናምን የሚሉትን ከመጀመሪያው ያገደ አምባገነን ሲሆን አሁን ያሉት ግን እነዚህን በንድፈ ሃሳብ ፈቅደው መሬት ላይ ስትተገብር ሲያገኙህ የተለያየ ስም እየሰጡ ባደባባይ ይገድላሉ፣ያስራሉ፣በተለያየ የማሰቃያ መንገዶችን ተጠቅመው ንፁሃንን ያሰቃያሉ፡፡ ደርግ ባደባባይ ንፁሃንን ገሎ በቴሌቪዥን መስኮት ቀርቦ ያለምንም ማመንታት ለምሳ ያሰቡንን ለቁርስ አረግናቸው ይላል፡፡ ዘመነኞቹ ጭራቆች ደግሞ ንፁሃንን ባደባባይ ግንባር ግንባራቸውን መተው የአደባባይ ላይ ነውጠኖች ይሏቸዋል፡፡ ንፁሃኖቻችንን አስረው በሬ ወለደ ዶክመንተሪ በመስራት ሽብርን የሚጠየፉ ንፁሃንን ሽብርተኛ ይሏቸዋል፡፡ ለዚህ ይመስላል ከያኒው ‹‹አዲስ ንጉስ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ ሲል›› ያዜመው፡፡ 


ከምርጫ 1997 በኋላ ይህ በይፋ የተገለጠበት እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ በእርግጥ በጊዜው ነገሮችን በጥልቀት ባልረዳም በሂደት ስለነበረው ነገር እንደተረዳውት የደርግን ጭራቅነት ሰው በላነት ሲነዙ የነበሩ ገዢዎች የስም ለውጥ በማድረግ እነሱ ቦታውን እንደተረከቡ ነው፡፡ እነዛ ብርቱ ዜጎች ለውጥንና ለውጥን ናፍቀው ከገኚዎች የተሰጣቸው ግን አፈሙዝ ነው፡፡ እነዛ ብርቱዎች ባጭር የተቀጩበት፤ፍትህ ዲሞክራሲ የናፈቃቸው፣ ናፍቋቸውም ይህ በአገራቸው እውን እንዲሆን የተነሱ ቆራጦች፡፡ የሰኔ 1997 ሰማእታት አስር አመታት ሞላቸው፡፡ አሁንም ግን የተመኙት፣የተነሱለት ከግብ አልደረሰም፡፡


አሁንም ግን የዘመናት ተጋድሎው እውን እንዲሆን በርካቶች እየታገሉ ይገኛሉ፡፡ በዚህም ስቃይ እንግልት እስራት ሞት አሁንም ቀጥሏል፡፡ በእርግጥም ያንቀላፉት ሰማእታት እራዕያቸው ከግብ የሚደርሰው የተነሱለት አላማ ግቡን ሲመታ ነው፡፡ ዘመነኞቹ ብርቱዎች አሁንም ትግላቸውን አላቆሙም፡፡ ይህ ግቡን እስኪመታ ድረስ አይቆምም፡፡ የሰማእታት አላማ ተራ አለመሆኑን ይህ ይገልፅልናል፡፡ ዘመን ተሻጋሪም ነው፡፡ ጉዳዩ ይህን ያህል ሰው ተከተለው ይህን ያህል ሰው አልተከተለው ሳይሆን ጉዞው አለማቆሙ ነው፡፡ ይብላኝ ትላንት የደርግን ጭራቅነት ሲሰብኩን ለነበሩ ዳግማዊ ጭራቆች መጨረሻ! ሰማዕታቱስ የተሰዉት ዘመን ተሻጋሪ አላማ ስላነገቡ ነው፡፡
ክብር ለሰማዕታት!