Thursday, 15 October 2015

ሰውነት ከበደን!


የመፃፍ ፍላጎት ብዙም አልነበረኝም ነገር ግን እዚሁ ፌስ ቡክ ላይ የማያቸው የአጥር ውስጥ ጫጫታዎች ከዛም ከፍ ሲል እንቶ ፈንቶዎች ከዛም ከፍ ሲል ሌላው ባዘጋጀው አጀንዳ ተከትሎ መትመምን ስመለከት በተለይ ከተደራሽነት አንፃር እንዲሁም አገር ውስጥ ባለው አፋኝ ስርዐት አማካኝነት በተለይም ሃሳቦችን ለማንሸራሸር የሚውሉ መድረኮች በመዘጋታቸው ሶሻል ሚዲያው ይህን ክፍተት ሙሉ በሙሉ መዝጋት ባይችልም እንደ አንድ አማራጭ መሆን ይችላል የሚል ግምት ነበረኝ፡፡ ነገር ግን እንደምናየው የተለያየ አጥር ውስጥ በመግባት እና እዛችው አጥር ውስጥ ሆኖ ወደ ውጭ ሆኖ በማጮለቅ ሆኗል ጫጫታው፡፡ ፌስ ቡክም የዚህ ጫጫታ መድረክ ሆኗል፡፡


ከላይ ጫጫታ ያልኩት የተለያዩ ሰዎች የሚያነሱትን ሃሳቦች ለማሳነስ ሳይሆን ሁኔታውን የሚገልፅ ከዚህ የተሻለ ቃል ስላላገኘሁ ነው፡፡ እስከሚገባኝ በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ለመስማማትም ሆነ ላለመስማማት መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ መናገር ብቻውን መነጋገር አይደለም፤ ሌላው የሚናገረውን መስማት ብቻውን መነጋገር አይደለም፡፡ ሁለቱም ተመጋጋቢ ሲሆኑ መነጋገር ይኖራል ከዛም ወይ መስማማት ይኖራል ወይ አለመስማማት ይኖራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አንድን ውይይት ለማድረግ የሆነ አጥር ውስጥ ሆነን ከሆነ ከመጀመሪያው ውይይቱ ከሽፏል፡፡ የብሔር በሉት፣የሐይማኖት በሉት አልያም የድርጅት አጥር ውስጥ ሆኖ ውይይት ቢደረግ ከጫጫታ ከፍ ያለ ትርጉም የለውም ለኔ፡፡


በዚህ መንገድ ብንቀጥል ከጫጫታ በቀር የምናተርፈው ነገር የለም፡፡ ይህን ስል ግልፅ ለማድረግ የምፈልገው ነገር ሰዎች ሃይማኖታቸውን፣ የመጡበትን ነገድ አልያም ሌላ አጥር ጥቀሱልኝ መዉደዳቸው ጤናማ ነው፡፡ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር እንዲሁም ፍሬያማ እንዲሆን እራሳቸውን ከአጥራቸው ማውጣት ያስፈልጋቸዋል፡፡ እያየን እንዳለነው ይህ ሳይሆን የሚደረጉ ጫጫታዎች የአንድ ሰሞን ጫጫታ ከመሆን አልዘለሉም፡፡ እስኪ ወደኋላ ተመልሳችሁ አስቡ እስኪ እዚሁ ፌስ ቡክ ላይ ስንት ጫጫታዎች አለፉ? በየትኞቹ ላይ ተግባባን? በየትኞቹ ላይስ ተነጋገርን? ካልን እንኳን መግባባታችንን ርዕሶቹን ማስታዎስ ይከብደናል፡፡


መረዳት እንደሚቻለው የኢትዮጵያ ጉዳይ ከአለም የተለየ ሆኖ አይደለም ይህን ያህል የምንወዘጋገበው፣ይህን ያህል ምጣችን የሚረዝመው፡፡ አሁንም ሆነ ነገ ከፋፋይና አምባገነን ገዢዎች በቀደዱት ዘው እያልን እንደጅረት የምንፈስ ከሆነ የአምባገነኖች ቤተ ሙከራ ከመሆን ምናልባት ትንሽ እድል ከንቶን በአጥራችን ውስጥ ትናንሽ ጌቶች እንሆን ይሆናል እንጂ ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት አንችልም፡፡ ስለሆነም በመንገዳችን ሌሎች በቀደዱልን ሳይሆን እራሳችን ባስቀመጥነው መንገድና አጀንዳ መንቀሳቀስ ይኖርብናል፡፡ ሌሎች ለኛ አጀንዳ እየቀረፁ እኛ በነሱ አጀንዳ እየተመምን ለውጥ የምናመጣ የሚመስለን ካለን ቆም ብለን ማሳብ ያስፈልገናል፡፡


በእውነት ለመናገር በዚህ ዘመን የከበደን ሰው መሆን ይመስለኛል፡፡ ያለቅድመ ሁኔታ የእኛን ሰውነት ተቀብለን የሌላውን ሰውነት መቀበል፡፡ እስኪ በሰሜኑ ሂዱ በደቡቡ ሂዱ በኢትዮጵያ ያለው ችግር ተመሳሳይ ነው፡፡ በጋራ የገጠመንን ችግር ከስሜትና ከአጥራችን በመሻገር እንደመፍታት አንዳንዴም ለስንፍናችን የተላያዩ የዳቦ ስሞችን እያወጣን እንዲሁም አጥራችን ውስጥ ሆነን እየተንጫጫን መቀጠሉን መርጠናል፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮማ የአንድን ሰው ሃሳቦች ነጥሎ ከመመልከት ይልቅ እስከ አያቱ መቁጠር እንዲሁም ፍረጃ ማካሄድ ባላስፈለገ ነበር፡፡፡ ሌሎች የሰጡትን ሳያላምጥ የሚውጥ ትውልድ ከዚህ መሻገር አይችልም፡፡


ሰብአዊነት ድምበር ተሻጋሪ ነው፡፡ ያ ባይሆን ኖሮ እነ አምንስቲ፣ እነ ሂዩማን ራይትስዎች የተሰኙ የመብት ተማጋቾች በርካታ ማይልሶችን አቋርጠው ስለኢትዮጵያውያን የመብት ጥሰትና የእስረኞች ኢ-ሰብአዊ አያያዝ ባልተጨነቁ ነበር፡፡ እኛ ግን አጥራችን ውሰጥ ሆነን የሌላው ህመምና ስቃይ የእኛም መሆኑን ዘንግተን በአጥራችን ውስጥ ተከልለን እራሳችንን የነገ ባለተረኞች ለማድረግ እንኳትናለን፡፡ ይህን ሁሉ ዘመን ተጉዘን የሰውነት ደረጃ ላይ መድረስ እንዴት አቃተን? የዘመኑት አገራት ቋንቋችንን ሳይጠይቁ የመጣንበትን ነገድ ሳይጠይቁ ወደ አገራቸው እያስገቡ ከዜጎቻቸው እኩል ሲያኖሩን እኛ ስለምን የገዛ ዜጎቻችንን የዚህ ቋልቋ ተናጋሪ ስለሆኑ እያልን ለአመታት ከኖሩበት ቀዬ ማባረርን መረጥን? ፈልገንና ወደን ባላጠለቅነው የማንነት ካባ እስከመቼ እየተቧደንን እንዘልቃለን? በዚህ ሁሉ መሃል ምጣችን ምን ያህል ይረዝም ይሆን? ሰውነትስ ከብዶን እስከመቼ?