ሰሞኑን በተከታታይ ሰማያዊ ፓርቲን አስመልክቶ በተነሳው ጉዳይ ሃሳቦች ሲሰነዘሩ እንዲሁም የጃጀው የፍረጃ ባህል አብሮ ሲነሳ ተመልክተናል፡፡ ከዚህ ቀደም ተደጋግሞ እንደተባለው ግልፅነትና ተጠያቂነት ለተቃውሞ ጎራው የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ቁም ነገሩ ዛሬ ተሰብስበን ነገ መበታተናችን አይደልም፡፡ በመንገዳችን አስር ጊዜ ልንወድቅና ልንነሳ እንችላለን ነገር ግን ካለፈው ምን ይዘን መጣን? ከውድቀታችንስ ምን ተማርን? ነገስ የትኛውን መንገድ እንመርጣለን? ያሰብንበት እንድንደርስስ የትኛው መንገድ ይጠቅመናል? የሚለው መመለስ ያለበት ነው፡፡
ፕሮፍ መስፍን በአንድነት ፓርቲ መስራች ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እንዲህ ብለው ነበር፡፡ ‹‹እንችላለን! እቺን አገር መለወጥ እንችላለን፤ ይቺን አገር ለመለወጥ ግን እያንዳንዳችን መጀመሪያ በቅድሚያ እራሳችንን መለወጥ አለብን፡፡ ፓርቲ ውስጥ የምንገባው እዚህ ወንበር ላይ ለመቀመጥ እዚያ ወንበር ላይ ለመቀመጥ ዝና ለማትረፍ አይደለም፡፡ ይሄንን እዚህ ፓርቲ ወስጥ ሰዎች ሲገቡ ጭንቅላታቸው ውስጥ አንጎላቸው ውስጥ የራሳቸውን ምስል ከተውበት ከሆነ የሚመጡት ሌላ ነገር አይገባም፤ቦታው ተይዟል፡፡ እዚህ ፓርቲ ውስጥ የሚገቡ ሰዎች የኢዮጵያን ህዝብ ነው፤ ኢትዮጵያን ነው አይምሯቸው ውስጥ አድርገው ነው መምጣት ያለባቸው፡፡ ማገልገል ነው አላማችን፤የኢትዮጵያን ህዝብ የአገሩ ባለቤት፣ የስልጣን ባለቤት ለማድረግ ነው፤ እኛ ባለስልጣን አንድንሆን አይደልም…››
ፍላጎታችን ወደ ስር ነቀል ለውጥ መሄድ ከሆነ የጃጀውን መንገድ መሻገር ይኖርብናል፡፡ አንድ የፓርቲ አባል አልያም ሊቀመንበር የማይከሰስና የማይጠየቅበት ሁኔታ የለም፡፡ አዲስ አድማስ ላይም ሆነ ሪፖርተር ላይ የወጡት ዜናዎች ላይ ቅሬታ ያለኝ ችግሩን በውስጥ የቱንም ያህል እርቀት ተሂዶ መፍትሄ መስጠት እየተቻለ ተቻኩሎ በሚዲያ እንዲወጣ በመደረጉ እንዲሁም የተጠቀሙት አላስፈላጊ ቃላት አንጂ ግለሰቦቹ ለምን ተጠየቁ ከሚል አይደለም፡፡ በመሪነት ላይ ያሉ ግለሰቦች መጠየቃቸው እንደውም ትልቅ ነገር ነው ብዬ ነበር፡፡ ይሄን በበጎ መመልከቱ ጠቃሚ ነው፡፡ ይህ በውስጥ ያለውን የዴሞክራሲ ባህል ነው የሚያሳየው፡፡ ይህ እንዲበረታታ አሁን ካለበት ከፍ አንዲል ነው ማገዝ የሚኖርብን፡፡
አንዳንዶች ከላይ ካለው በተቃራኒ ስለ ግለሰቦች ሲያለቅሱ ነበር፡፡ ይሄ በቀጣይነት ምን ይዞ እንደሚመጣ ማሰብ የፈለጉ አይመስሉም፡፡ በጓደኝነት በሌላም በሌላም ምክንያት ጠበቃ ሁነው ሌላው ላይ ፍረጃ ሲያካሂዱ ይታያል፡፡ይህ የተካበውን ከማስፍረስ ውጪ አንዳችም የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ ግለሰቦቹንም ሆነ ፓርቲውን አንጠቅምም፡፡ የፍረጃ ትልቁ ችግር ወርቃማውንና ስልጡኑን በመከባበርና በእኩልነት ቁጭ ብሎ የመነጋገር እድልን መዝጋቱ ነው፡፡ ሌላው ለተቃውሞ ጎራው እንቅስቃሴ አድሮ ቃርያ መሆን ትልቁን ሚና የሚጫወተው የግለሰብ አምልኮ ነው፡፡ ከዚህ መውጣት መቻል ይኖርብናል፡፡ መነጋገርም መጠየቅም ካለብን በእኩልነትና በሰለጠነ መንገድ መሆን አለበት፡፡ የሊብራል ዲሞክራሲን አስተሳሰቦች እንከተላለን እያልን በጉያችን የጌታና ሎሌ ግንኙነት ይዘን የትም አንደርስም፡፡ በቅድሚያ ይህ ማብቃት ይኖርበታል፡፡
በፓርቲ ውስጥ ያሉ የትኞቹም ክፍሎች ደካሞች ቢሆኑ ለፓርቲው ምን ይጠቅማሉ? ጥርስ የሌለው ብሄራዊ ምክር ቤት፣ጥርስ የሌለው የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን ምን ይስራል? ስለዚህም ለእነዚህ አካላት ስልጣን ሰጥቶ ለምን ጠየቁ፣ለምን ከሰሱ፣ ለምን ውሳኔ አሳለፉ ብሉ ማልቀስ አሮጌውን መንገድ ባዲስ ቅላጼ ይሆንብኛል፡፡ ለዚህም መልሱ ፍረጃ አልያም ይህንን ፅሁፍ እየፃፍኩ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ተስብስቦ የፓርቲው የስነስርዐት ኮሚቴ ያሳለፈውን ውሳኔ ሽረነዋል ማለት ዳግም ስህተት ውስጥ መግባት ነው፡፡ ለስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ይህን ስልጣን ማን ሰጠው? ይህ ነገ ምን ይዞ እንደሚመጣ አላወቁም…
ለአራቱ ግሰቦች ከፓርቲው መባረርም ሆነ ለሌሎች ጉዳዮች የፓርቲው መተዳደሪ ደንብ መፍትሄዎችን በግልፅ አስቀምጧል፡፡ ምዕራፍ ስድስት ጥፋቶችና ውሳኔ አሰጣጥ በሚል ርዕስ ከአንቀፅ 41 ጀምሮ እስከ 49 ይዘረዝራል፡፡ አንቀፅ 49.1 እንዲህ ይላል፡፡ የስነ-ሥርዓት ውሳኔው ተግባራዊ የሚሆነው ይግባኝ ሂደቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ነው፡፡ ማንኛውም ውሣኔ የተወሰነበት ወገን ውሳኔው በይግባኝ እንዲታይለት የሚፈልግ ከሆነ በ15 ቀን ጊዜ ውስጥ ይግባኝ ማቅረብ አለበት፡፡ በመጨረሻ ላይ አንቀፅ 49.11 ላይ በፓርቲው የሥነ-ሥርዓት ኮሚቴና በፓርቲው የይግባኝ ሰሚዎች ውሳኔ የማይስማማ አካል በመደበኛ ፍርድ ቤት ክስ የመመስረት መብቱ የተከበረ ነው፡፡ እስኪ እስቡት ተባረሩ የተባሉ ግለሰቦች ከዚህ ውስጥ የትኞቹን መንገዶች ነው እስከ ጥግ ድረስ የሄዱባቸው? ነገስ የትኛውን ይመርጣሉ? የትኛውስ መንገድ የተቃውሞ ጎራውን አድሮ ቃሪያ ከመሆን ይታደገዋል?