Tuesday, 23 August 2016

የስርዐቱ የይቅርታ ካርድ እየመሸበት ይሆን?



ስርዐቱ ከምርጫ 97 በኋላ በተለይም የፖለቲካ አመራሮችን፣ጋዜጠኞችን በአመለካከታቸው ከስርዐቱ በተቃርኖ ስለቆሙ ብቻ ወደ ማጎሪያዎቹ የሚያስገባቸውን ንፁሃን ባላጠፉት ጥፋት ከሶ የፍርድ ውሳኔ ካስተላለፈባቸው በኋላ በውስጥም በውጭም  ግፊት  ሲበረታበት ለፖለቲካ ትርፉ ሲል የይቅርታ ካርድ ይመዝና ከእስር ያስወጣቸዋል፡፡ ለዚህም በቅንጅት አመራሮች እንዲሁም በብርቱዋ የፖለቲካ መሪ ወ/ሪት ብርትኳን  ሚደቅሳ የሆነው ለዚህ ሁነኛ ማሳያ ማሳያ ነው፡፡



 እቺ ‹‹ይቅርታ›› የሚሏት  የመጫወቻ ካርድ በገዢዎቹ አተረጓጎም የስሟን እሩብ እንኳን የማትመዝን በተለይም ታሳሪዎቹ ከእስር ከተለቀቁ በኋላ ዳግም ወደቀድሞ እንቅስቃሴያቸው ቢገቡ እንደማስጠንቀቂያ  እቺው የይቅርታ ካርድ ተመዛ ወደ እስር እንደሚወረወሩ ማስፈራሪያም ጭምር ናት፡፡ ሌላው በምርጫ ዘጠና ሰባት እንደታየው ስርዐቱ ኮሮጆ ገልብጦ ተቃውሞ ሲበረታበት የቅንጅት አመራሮችንና ጋዜጠኞችን ጠራርጎ አስሮ የህዝብን ጥያቄ ከድምፃችን ይከበር ወደ መሪዎቻችን ይፈቱ ዳይቨርት በማድረግ በመጨረሻም በአቶ በረከት አገላላፅ ከናዳው ለማምለጥ እስርና እቺኑ የይቅርታ ካርድ ተጠቅሟል፡፡  በቀጣይ ጊዜም እቺኑ ካርድ  በተመሳሳይ መንገድ ለፖለቲካ መሪዎች እንዲሁም ለጋዜጠኞች እንዲሁም ለሓይማኖት መሪዎች ጭምር ለመጠቀም ተሞክሯል፡፡



ይህ ሁኔታ በጋዜጠኛና መምህርት ርዕዮት አለሙን በተመሳሳይ መንገድ ከእስር እንድትወጣ የተደረገው ውትወታና በእስር ቤት  ይደርስባት የነበረውን  ተፅእኖን ተቋቁማ ባላጠፋችው ጥፋት ይቅርታ እንደማትጠይቅ  አስረግጣ በመንገር የስርዐቱን ሴራ በማክሸፍ የእስር ጊዜዋን ጨርሳ ወጥታለች፡፡ ከዚህ ጊዜ በኋላ የስርዐቱ የይስሙላ የይቅርታ  ካርድ  እየመሸባት ስለመሆኑ ሌላው ማሳያ የሙስሊሙ ህብረተሰብ ጥያቄ ነው፡፡



ስርዐቱ ህዝበ ሙስሊሙ ከመረጣቸው የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ጋር ሲነጋገር ቆይቶ ጥያቄው እየሰፋ ሄዶ በክልል ያለውን ህዝበ ሙስሊም ማነቃነቅ ሲጀምር  የኮሚቴው አባላትን  በማሰር ጥያቄውን ዳይቨርት ለማድረግ  ቢሞከርም እንዲሁም የኮሚቴው አባላት በተመሳሳይ የይቅርታ ካርድ ተመዞ ከእስር እንዲፈቱ ቢጠየቁም ፈቃደኛ ሳሆኑ ቀርተዋል፡፡ የሙስሊሙ ድምፃችን ይሰማ  እንቅስቃሴ መሪዎቻችን ይፈቱ የሚለውን ጥያቄ ለይቶ ከማስተጋባት ይልቅ ቀድሞ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ከጠየቃቸው ሶስት ጥያቄዎች በመቀጠል አራተኛ አድርጎ በመጠየቅ አሁን ካለበት ደርሷል፡፡

 
የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን እና የጦማሪኑን እስር ተከትሎ ለማሳያነት  የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን የተወሰኑም ቢሆን ክሳቸው ተቋርጦ በነፃ ሲሰናበቱ ሌሎች በውጭ በመሆን ጉዳያቸው እየታየ ነው፡፡  በቅርቡም የአንድነትና የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች  ጊዜያቸውን ጨርሰው ከእስር ሲፈቱ፤ የአረና ፓርቲው አብርሃ ደስታ ከወራቶች በሁዋላ የእስር ጊዜውን ጨርሶ ከእስር አንደሚወጣ ታውቋል፡፡ በእርግጥ አሁን ላይ ሁኖ የስርዐቱ የይቅርታ ካርድ መሽቶበታል  ብሎ መደምደም አይቻል ይሆናል፡፡ ይህ በተለይም በተቃውሞ ጎራው ውስጥ  ያሉ አባላትና አመራሮች ሲታሰሩ እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ፓርቲ እንዲሁም በአገሪቱ ባጠቃላይ የፍትህና የዲሞክራሲ ጥያቄዎችን ተከትሎ ለሚመጡ የገዢዎች ጅምላ እስር የሚሰጠው ግብረመልስ ወሳኝነት ይኖረዋል፡፡
01/09/08

ስር ነቀል ለውጥ!



ባለፈው ፖለቲካችን በተለይም የስልሳቹ ትውልድ በፖለቲካው በኩል ያደረገው ትግል እንዲሁም የተገኘውን ውጤት ስናይ ከተከፈለው መስዋትነት ጋር ፈፅሞ ሊገናኝ የማይችል ሆኖ እኛገኘዋለን፡፡ በተለይም ትግሉ ጠያቄ የሆኑ ወጣቶቻችንን ቅርጥፍ አድርጎ በመብላቱ አሁን ላይ አደባባዩ ላይ እውቀት ሳይሆን ድፍረት ያላቸው ሆድ አደሮች ቦታውን እንዲፈነጩበት ሆኗል፡፡ ይህም ለውጡን ስር ነቀል ከማድርግ ይልቅ አንዱን አምባገነን በሌላው በመተካት በሳዛኝ ሁኔታ ተጠናቋል፡፡



ደርግ ወርዶ ዘመነኞቹ ከፋፋይና አምባገነን መሪዎች ስልጣን ከተቆጣጠሩ ጀምሮ እንዳለፈው አቻቸው በግልፅ በቴሌቭዢን መስኮት ቀርበው ‹‹ለምሳ ያሰቡንን ለቁርስ አረግናቸው›› አይበሉን እንጂ መግደሉና ማሰሩ የእለት ተለት ተግባራቸው ነው፡፡ በተለም በአገሪቱ ውስጥ ለሚነሱ የመብት ጥያቄዎች እስካሁን ድረስ ከጠብ-መንጃ የተሻለ መልስ አልሰጡም፡፡ ዛሬም ኢትዮጵያውያን ለሚያነሱት የመብት ጥያቄዎች መልሱ የጅምላ እስር፣ ሞትና ስደት ሆኗል፡፡



አሁንም ቢሆን ለውጥ ወዳድ የሆኑ ግለሰቦች የሚሄዱበትን መንገድ ደግመው ደጋግመው ሊፈትሹ ይገባል፡፡ ቤት ለቤት የደረሰውን የስርዐቱን  አፈና እንዲሁ በአንድ ለሊት አሸንፎ መውጣት ይቻላል የሚል ቅዠት ውስጥ በፍፁም ሊገቡ አይገባም፡፡ ምክንያቱም ትግሉ የሚካሄደው ከገዢዎች ጋር ብቻ አይደለምና፡፡ እንዲሁም የሚከፈለው መስዋትነት እንዳለፈው አንዱን ጨቋኝ በሌላው ጨቋኝ መተካት ሳይሆን  ፖለቲካውን ከጉልተኛውና ከደብተራው ባህል አላቆ፣ ከሆዳምነትና ከግላዊ የከንቱነት ስሜቶች፣ ከእብሪት እና ከማን አንሼ ባይነት አፅድቶ በምክንይት ላይ የቆመ የነፃነት፣ የብልፅግና፣የእውቀት፣የእኩልነት እና የፍትህ መሳሪያ በማድረግ ማዘመን ነው፡፡



ይህንን ደግሞ ገዢዎቻችን በቀደዱልን መንገድ ተጉዘን እንሞክረው ብንል  እዛው ከመርገጥ ውጭ ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት አይቻለንም፡፡ መሆን ያለበት የገዢዎችን የከፋፍለህ ግዛ አጥር ሰብረን በመውጣት መሰረታችንን ሰብአዊነት ላይ በማድረግ በአንድነት መነሳት ይኖርብናል፡፡ ካለበለዚያ ገዢዎቻችን በቀደዱልን ፈሰን ለየብቻ የምንጮህ ከሆነ እራሳችንን ለገዢዎቻችን በትር እንዲመች አድርገን  አዘጋጅተናል  ማለት ነው፡፡ ስለሆነም የመብት ጥያቄዎች ይህ አካል ወይም የዚህ ቋንቋ ተናጋሪ ስላነሳቸው ሳይሆን  መሰረቱ ጥያቄው ነው መሆን ያለበት፡፡

የስርዐቱ ኢ-ፍትሃዊ እና  አደህይቶ መግዛት በመላ አገሪቱ እየተተገበረ ያለ  ነው፡፡ ለምሳሌ በጋምቤላ ሰፋፊ መሪቶችን ለውጭ አገር ባላሃብቶች እየሰጡ  በሰፈራ ስም ነባሩን ገበሬ ከሰፋፊ ቦታዎቹ እያፈናቀሉ አንድና ሁለት ከብት እንኳ ማኖር በማያስችል ጠባብ መሬት እንዲቀመጥ ያስገድዱታል፡፡ በጉራፈርዳ የሚኖሩ የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ላይ አገራችሁ አይደለም ተብለው ያፈሩት ንብረት ተዘርፎ፣የተወሰኑት ተገድለው የተቀሩት ባዶ እጃቸውን ወጥተዋል፡፡ አሁን ተማሪዎች ተቃውሞ እያሰሙ ያሉትም በኦሮሚያ ልዩ ዞን ያሉ ቦታዎችን ወደ አዲስ አበባ ማካለል በሚል አንዱን በማደህየት ሌላውን ማደለብ ነው፡፡ የስርዐቱን ኢ-ፍትሃዊ ድርጊት  እንዲህ እንዲህ እያልን ብዙ መጥቀስ እንችላለን…




መረሳት የሌለበት ይህ ስርዐት እስካለ ድርስ ዜጎችን ማፈናቀልና አደህይቶ መግዛት ይቀጥላል፡፡ አሁን ተቃውሞ እየቀረበበት ካለው ማስተር ፕላን  ጥንስስ በፊት በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ሰፋፊ መሪቶች እንደጉድ ተቸብችበዋል፡፡ ነዋሪዎቹ ተፈናቅለው  ለቦታቸው ምትክ በሚል የሚሰጧቸው ገንዘቦች ከፋፋዮቹ ገዢዎችና የእነሱ የጥቅም ፓርትነሮች ከሚያገኟቸው አንፃር ሲታይ የብላሽ አይነት ነው፡፡ ስለሆነም ስርአቱ እስካለ ድርስ እስሩ፣ስደቱ ሞት እና  እና ኢ-ፍትሃዊ ድርጊት ይቀጥላል፡፡ የለውጡ ዋና አላማም በየትኛውን ብዱን ላይ መነሳት አልያም ጥላቻ ሳይሆን በመሰረታዊነት ከአገዛዝ ቀምበር በመውጣት ወደ ዲሞክራሲ የሚያስኬደውን ይህም ሁላችንንም በጋራና በእኩልነት ወደሚያስተዳድር ስርዐት ማምራት ነው፡፡



ይህም ጉዞ የተሳካ የሚሆነው የተወሰነ አካል አልያም ቡድን  ሞቶ ሌላውን ነፃ ለማውጣት ሳይሆን እያንዳንዱ  ዜጋ ገዢዎቹ ያነበሩበትን ጭቆና አራግፎ በመጣል እራሱን የለውጡ አካል በማድረግ የበኩሉን ሲያደርግ ነው፡፡ ይህም ከለውጡ በኋላ ስርነቀል ለውጡ እንዳይቀለበስና የባለቤትነት ስሜት ተሰምቶት በንቃት እንዲጠብቅ ያስገድደዋል፡፡ ሁሉም ግዴታ የድርጅት አባል ይሁን ባይባልም ባለበትና በተሰማራበት ቦታ ሁሉ የገዢዎችን የጭቆና ቀንበር አራግፎ  በመጣል ትግሉ  በዋነኝነት ተቋማዊ መሰረት አንዲይዝ መታገል አለበት፡፡ በእርግጥም የትውልዱም ሆነ የለውጥ ወዳዱ ዜጋ ዋነኛ ጭንቀት ስርአቱን ከስልጣን ማውረድ አይመስለኝም ምክንያቱም ስርቱ የትጋት ጊዜውን ጨርሶ የልግመት ጊዜ ላይ ነውና! መውረዱ የማይቀር ነው፡፡ ዋነኛው  ጉዳይ ከአገዛዝ ወደ አገዛዝ ሳይሆን ካገዛዝ ወደ ዲሞክራሲ ነውና!
ጉዞ ወደ ፊት!

የተቃውሞ ጎራው…



 ለዚህ ፅሁፍ መነሻዬ በውይይት መፅሔት ‹‹የተቃውሞ ፖለቲካ ተስፋ አለው?›› በሚል ርዕስ የቀረበው ፊቸር ነው፡፡ በአዘጋጆቹ ለጥያቄ የቀረቡ  ነጥቦች አንዳንዶቹ በተለይም  በተቃውሞ ጎራው ላይ  ተደጋግመው የሚነሱም ናቸው፡፡ ወደ መፍትሄው ለመሄድ ግን ከነዚህ ነጥቦች ውጪ የሚሆን አይመስለኝም፡፡  ለዛሬው በተወሰኑት ላይ ብቻ ሃሳቤን እገልፃለሁ፡፡ ተደጋግሞ እንደሚባልው የፓርቲዎች ቁጥር መብዛት መነጋገሪያ መሆኑ አልቀረም፡፡ 75 የሚጠጉ ፓርቲዎች መኖራቸው ሲነገር ቆይቷል፡፡ በቅርቡ ምርጫ ቦርድ 14ቱን  መሰረዙን ሰምተናል፡፡ እንደኔ የፓርቲዎቹ መኖር ሰርተፍኬቱን ይዞ ከመቀመጥ ውጪ ከጥቂቶች በስተቀር  መሬት ላይ የሚወርድ ስራ የሚሰሩ አይደሉም፡፡ በዚህ መክንያት በምርጫ ሰሞን እየመጡ ህዝብን ግራ ከማጋባትና  የአሯሯጭነት ሚናቸውን  ከመወጣት ውጪ  ፋይዳ ያለው ሚና የላቸውም፡፡ ስለሆነም ቁጥራቸው መኖሩ ብቻውን ፓርቲዎቹ አሉ ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም በተግባር መሬት ላይ የሉምና!

ሌላው የተነሳው የተቋማዊነት ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ መሬት የሚወርድ ስራ የሚሰሩ የለውጥ ሃይል የሆኑ ፓርቲዎች በፓርቲያቸው ውስጥ የዲሞክራሲ ባህል እና ተጠያቂነትን የሚያሰፍን አካሄድ መከተል የህልውና ጉዳይም ነው፡፡ የተወሰደው ጊዜ ተወስዶ ጠንካራ  ተቋማዊ መሰረት እንዲይዙ ካልተደረገ  የተቃውሞ ጎራው ነገ መንግስት ሊሆን የሚያስችለውን አቅም መገንባት አይችልም፡፡ አሁን ያለውን ሁኔታ ምሳሌ ማቅረብ ይቻላል፡፡ በገዢው ፓርቲ በኩል ጥቅምም ሃይልም አለ፡፡ በተቃውሞ ፖለቲካው ውስጥ ይህ የለም፡፡ ለምሳሌ አንድ ግለሰብ የሰማያዊ ፓርቲ አባል ሲሆን እነዚህን ነገሮች ታሳቢ አያደርግም፡፡  ከዚህ ይልቅ የሰማያዊ ፕሮግራሞችን መሰረት አድርጎ ነው አባል የሚሆነው፡፡ በተለያየ ምክንያት ከፓርቲው ሲለቅም የሚያጣው ጥቅምም ሆነ በመልቀቁ ምክንያት የሚደርስበት ጉዳት የለም፡፡

በዚህ የተነሳ በተለይ በግለሰቦች መካከል የሚነሱ እሰጣገባዎችና  ችግሮች ምክንያት ፓርቲዎቹ ተናከሱ ተብላሉ ሲባል መስማት የተለመደ ነው፡፡ይህ በዋነኝነት የሆነው የውስጠ ዲሞክራሲውን እንደመጨረሻ በማየት ሲሆን ይህ የውስጠ ዲሞክራሲ መኖር ግን በጠንካራ ዲሲፕሊን ካልታገዘ  አንዳለፈው በውስጥ ያለውን ዲሞክራሲ ያለአግባብ  በመጠቀም  መካሪ አልባ ፖለቲከኞች ሊፈነጩበትና ትግሉንም የኋሊት ከመውሰድ የሚያግዳቸው አጥር አይኖርም፡፡ አሁን ባለችው ኢትዮጵያ ትግሉን ጨምሮ ለብዙ ነገር እንቅፋት የሆነው ተቋም አልባ አገር መያዛችን ነው፡፡ በዚህ ምክንት አሁን በተቃዋሚነት የሚገኝ ነገ የመንግስት ስልጣን ከመያዙ በፊት በፓርቲው ወስጥ ተቋማዊ መሰረት በመጣል ምሳሌ መሆን አለበት፡፡



ስርዐቱ ከጊዜ ወደጊዜ  እየወሰዳቸው የመጣቸውን የአፈና እርምጃዎች ተከትሎ የተቃውሞ ጎራውን ትግል እጅግ ፈታኝ አድርጎታል፡፡ ይህ የሚስተባበል ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህ መሆኑ ቢታመንም ከዚህ ገሸሽ ማለት የሚያመጣው ለውጥ የለም፡፡ ከዛሬው በበለጠ ችግሮች ተደራርበው ይጠብቁ ይሆናል እንጂ  ችግሮቹ በራሳቸው መፍትሄ ሆነው አይመጡም፡፡ ከችግሮቹ መፍትሄዎቹን መፈለግ ግን  የለውጥ ሃይሉ ድርሻ ነው፡፡ እዚህ ላይ ያለው አማራጭ ያሉትን ቀዳዳዎች በመድፍን ወደፊት መጓዝ ነው፡፡ ወደፊት  በሚደረጉ የተቃውሞ ጎራው እንቅስቃሴዎች በተቻለ መጠን  ካለፈው በመማር፤ የወደፊቱን አርቆ በመመልከት በጥልቀት ከተሰራ ተስፋ ያለው ውጤት የማናይበት ምክንያት የለም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ከሄድን መሬት ላይ ባለተሰራ ነገር ተስፋ የለምና ተስፋ ሰጪ ነገር  አይኖርም፡፡ ይህን የመወሰን ሃይል ያለው ስልጣን ላይ ያለው አካል ሳሆን ከብዙ ነገር በዘለለ የለውጥ ሃይሉ መሬት ላይ የሚስቀምጣት ተግባር ናት!
‹‹አዎ እንችላለን!›› ክቡር ገና

ከስርአቱ አንድ እርምጃ መሻገር!



እስከሚገባኝ ገዢዎቻችን በቀደዱት የምንፈስ ከሆነ እዛው ከመዳከር ውጪ አዲስ ነገር አንፈጥርም፡፡ ዛሬ ስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ትላንት ስልጣን ላይ ከመውጣታቸው በፊትም ሆነ ስልጣን ላይ ከተቆናጠጡ በኋላ በተለይ ያለፉትን መንግስታት አስታከው ስርዐቱ የአማራ ህዝብን ከገዢ መደብ ጋር ጨፍልቆ ለፕሮፓጋንዳው አውሎታል፡፡ በዚህም የተነሳ ደሃው ህዝብ  በየደረሰበት የጥላቻ ሰለባ ሆኗል፡፡  በዘመነ ስልጣኑ ያለውን ደግሞ ወጣቱ ፖለቲከኛ አንዷለም አራጌ ከቃሊቲ እስር ቤት ሆኖ በፃፈው መፅሐፍ  ‹‹ህወሓትና የትግራይ ህዝብ›› በሚል ርዕስ የፃፈውን እዚህ ላቅርበው 



‹‹አሁን ባለው የኢትዮጵያ አገዛዝ ውስጥ ዋናውን ሥላጣን የጨበጠው ህወሓት መሆኑን መካድ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ሌሎች ብዙም ትርጉም ያለው ሚና እንደማይጫወቱ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ህወሓት ደግሞ እንደስልጣን መሰረት የሚወስደው አፈ-ሙዝን ሲሆን የትግራይንም ህዝብ እንደ መያዣ(hostage) እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡ ጥቂቶች በጦርነት ወቅት የተከፈለውን መስዋትነት እየመነዘሩ ሥልጣን ላይ መቆየት ይሞክራሉ፡፡ ይኽን እውን ለማድረግ የትግራይን ህዝብ የሥርአቱ ልዩ ተጠቃሚ በማስመሰል ህወሓት ስልጣን ከለቀቀ የሌላ ብሔር ተወላጅ ወንድሞቹ ሊያጠፉት እንደሚነሱበት በማስፈራራት በትግራይ ህዝብና በሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ አለመተማመን እንዲነግስ ሆን ብሎ የተከለው መርዝ እያፈራለት ይመስለኛል›› 



ነገን የተሻለ ለማድረግ ፍላጎቱ ካለን የብሔር አጥርም ሆነ የፓርቲ አጥር ሊያግደን አይገባም፡፡ ይህን የምለው ለለውጥ ሀይሉ እንጂ ከአጥራቸው ላለመውጣት እራሳቸውን በጥቅምና በቁስ አምልኮ ምርኮኛ ላረጉት አይደልም፡፡ ስርዐቱን እቃወማለሁ የሚል የትኛውም አካል ቢያንስ ከስርዐቱ አንድ እርምጃ መሻገር ይጠበቅበታል፡፡ ለምሳሌ በጎንደር እና ደባርቅ በተካሄደው ተቃውሞ ተከትሎ ተደረገ በተባለው ነገር የሚነዛው ፕሮፓጋንዳ  በድጋፍም ሆነ በተቃውሞ ከጊዜያዊ የፖለቲካ ስሜት ተሻግረን ካየነው ተጠቃሚ የሚሆነው ህወሓት ነው፡፡ ለዚህ ነው በመነሻዬ ላይ እነሱ በሚቀዱት የምንፈስ ከሆነ እዛው ከመዳከር ውጪ አዲስ ነገር እንደማይፈጠር ለመግለፅ የሞከርኩት፡፡



ባንፃሩ ልዩት ሳያግደን ትኩረታችንን በዜግነት እና በዜግነት ላይ በማድረግ የስርአቱን ሴራ ማሸነፍ እንችላለን፡፡ በዚህም ከእከክልኝ ልከክልህ አገዛዝ በመሻገር በአገራችን የዴሞክራሲ ስርዐት መሰረት እንዲጣልና ሁላችንንም በዜግነታችን  የምታስተናግድ ኢትዮጵያ እንድትፈጠር ማድረግ እንችላለን!
አዎ እንችላለን!
ክቡር ገና!

ሰላም ምንድን ነው?



ደጋግመን እንደምንሰማው ሰላም ማለት የጥይት ድምፅ አለመሰማት እስኪመስል ድረስ ተደጋግሞ ሰላም፣ሰላም ይባላል፡፡ በዚህ መሃል  ንፁኃኑ ሃሰባቸውን በመግፃቸው ብቻ ወደ ማጎሪያዎቹ ይወረወራሉ፡፡ የሃይማኖት ነፃነት ጥያቄ ያነሱ ዜጎች የሽብር ታርጋ እየተለጠፈባቸው ይታሰራሉ፡፡ ፖለቲከኞች ከስርዐቱ በተቃርኖ በመቆማቸው ብቻ ይታሰራሉ፣ይንገላታሉ፣ይገደላሉ፣ይሰደዳሉ፡፡ መንግስትን ለመቃወም አደባባይ የሚወጡ ንፁሃን ዜጎች የጥይት እራት ይሆናሉ፡፡ ይህን ተከትሎ ከመንግስት ባለስልጣን እስከ ተራው ዜጋ ስለ ሰላም ያወራሉ፡፡ ልማታችንን ለማስቀጠልና ለማፋጠን ሰላም ወሳኝ ነው ይሉሃል፡፡ የቤተ እምነት ሰዎችም ይከተሉና ተመሳሳይ ነገር ይናገራሉ፡፡ በተመሳሳይ ጎንህ ጋር ያለውም ሰላም እፈልጋለሁ ይልሃል፡፡ እዚህ ጋር  ሰላም፣ ሰላም እየተባለ እዚያ ጋር ንፁሃኑ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው ይታያሉ እና ሰላም ምንድን ነው? የሚለው ጭንቅላቴን እያዞረው ከዚህ በታች ያለውን የፕሮፍ መስፍን ፅሁፍ አገኘሁ፤ እንደወረደ አቅርቤዋለሁ፡



ለብዙ ሰዎች ሰላም ማለት ጦርነት የሌለበት ሁኔታ ነው፡፡ ወገን ወይም ቡድን ለይተው ጦር መሳሪያ መዝዘው ካልተዳሙ፣ካልተቆሳሰሉና ካልተገዳደሉ ሰላም ነው ይባላል፡፡ ይህ ሁኔታ የሰላም ሁኔታ ላይሆን ይችላል፡፡ አንድ አባት ልጁን በጥፊ ወይም በለበቅ እየደበደበ ‹‹ጭጭ፣እስቲ ትንፍሽ!›› እያለ ማልቀስ እንኳን ቢከለክለው፣ ወይም አንድ ሰው አንድ ሌላ ሰው ደረት ላይ ቆሞ ትንፋሽ ቢያሳጣው፣አንድ ህዝብ በፖሊስና በጦር ሃይል ተሰንጎ ተይዞ ጭጭ ብሎ በደሉንና ጥቃቱን ቢችል ሰላም ነው ማለት አይደለም፡፡ኃይለኛ ደካማውን ሲያጠቃ ሰላም የለም፤ብዙዎች ጥቂቶችን ሲያጠቁ ሰላም የለም፤ጥቂቶች ተደራጅተውና ታጥቀው ብዙዎችን ሲያጠቁ ሰላም የለም፡፡ ጸጥ፣ለጥ ብሎ መገዛት ሰላም አይደልም፡፡

ጦርነት ባለመኖሩ ብቻ ሰላም አለ ማለት አይቻልም፡፡ ኃይለኞች ደካሞችን አስገብረው፣በጉልበታቸው የሰውን ልጅ መንፈስ ገድለው፣አእምሮው ታዛዥና ተገዢ ብቻ እንዲሆን አድርገው በድኑን አንደአሻንጉሊት በሚጫወቱበት ሁኔታ ሰላም የለም፡፡ እንኳን መሳሪያ አንስቶ ለመዋጋት መረረኝ፣ደከመኝ ለማለት የሰው ልጅ የመንፈስ ሃይሉ ተሟጦ በድን፣ የቁም ሬሳ ሆኖ በሚንገላታበት የአገዛዝ ስርዐት ውስጥ ሰላም የለም፡፡ በእንደዚህ አይነቱ ሁኔታ ውስጥ ጥላቻ፣ወፍራምና ልብን ሞልቶ የታፈነ ጥላቻ አለ፡፡ጥላቻ ክፉ ጦርነት ነው፡፡ የተጠቃ፣የተበደለ፣የተበዘበዘና የሰውነት ክብሩን የተገፈፈ ሰው በልቡ ውስጥ የታመቀው ጥላቻ እያደገ ጊዜና ሁኔታው ሲፈቅድለት ግፈኞችን ይዋጋል፡፡ ስለዚህ ግልጽና ገሃድ አይሁን እንጂ ጦርነት አለ፡፡ ከጥላቻና ከሚመግል ቂም የሚመነጨው የደካማዎች ጦርነት በይበልጥና በተጨማሪ ራስን በመጉዳት የሚደረግ ጦርነት ነው፡፡ ጊዜ ይፈጃል እንጂ ምንጊዜም ድል የደካማዎቹ ብዙኃን ነው፡፡



እንግዲህ ሰላም አፋዊ ጸጥታ ብቻ አይደለም ማለት ነው፡፡ ሰላም የውስጥና የመንፈስ ደስታና እርካታም ነው፡፡ ሰላም ለራስና ለሌሎች ሰዎች ሙሉ አክብሮት ሲኖር ነው፡፡ ሰላም በራስና በሌሎችም ሰዎች መካከልመተማመን ሲኖር ነው፡፡ ሰላም በአለው ህግና ስነ ስርዓት ላይ ሙሉ እምነት ሲኖርና በበጎ መንፈስ የራስን ችሎታ በማዳበር የግል ኑሮን ለመምራት የሚያበቃ ሁኔታ ሲኖር ነው፡፡ በአገራችን ብዙ ሰዎች የማይገነዘቡት ሌላ ነገር አለ፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ለጦርነት የሚከፈለውን ያህል ለሰላምም ይከፈላል፡፡ በሌላ አነጋገር ጦርነትን በነፃ ያለምንም ክፍያ ማካሄድ እንደማይቻል ሁሉ ሰላምንም ያለምንም ክፍያ በነፃ የሚያገኝ ህዝብ ወይም ኅብረተሰብ የለም፡፡ ለሰላም የሚከፈል ዋጋ አለ፡፡ ሰብአዊ መንፈስንና ሰብአዊ  ክብርን ጠመንጃ ላነገተ ሁሉ ባለመገበርና አሻፈረኝ በማለት የሚከፈል ዋጋ አለ፡፡ የራስንና የሌሎችን መብት ለማክበርና ለማስከበር የሚደረገው ጥረት ዋጋን ያስከፍላል፡፡ 



ለሰብአዊ ክብር፣ለእኩልነትና ለፍትህ፣ለነፃነትና ለመብት፣በአጠቃላይም ለሙሉ ሰላም ለሚደረገው ትግል ጨቋኞችም ተጨቋኞችም ተገቢውን ዋጋ ይከፍላሉ፡፡ የጭቆና ቀንበርን የተሸከሙት እንቢኝ አሻፈረኝ ብለው የእምቢተኛነታቸውን ዋጋ ሳይከፍሉ ከጭቆና አይገላገሉም፡፡ ጨቋኞችም በሰው ልጅ የመንፈስ ኃይል ተሸንፈው የጭቆና መሳሪያቸውን ካላጡ በጭቆና ላይ ከተመሰረተው የበላይነታቸው አይገላገሉም፡፡ ይህም ማለት በጨቋኝና በተጨቋኝ መሀከል ሰላም የሚሰፍነውና ጭቆና የሚጠፋው ጨቋኙ ዝቅ ብሎ ተጨቋኙ ከፍ ብሎ ሁለቱም በሰውነት ደረጃና በህግ ፊት እኩል ሆነው ሲቆሙ ብቻ ነው፡፡ ጭቆናና የጭቆና መሳሪ እስካለ ድረስ ሰላም አይኖርም፡፡
ምንጭ; ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም 1986 ኢትዮጵያ -ከየት ወዴት?  ገፅ 81-82




‹‹በሰለጠነ አገር በምቾትና በድሎት እየኖሩ… ሰላማችንን ለማደፍረስ…››

በኮሚዩንኬሽን ጉዳዮች የተሰራጨ እንደሆነ ያደመጥኩት እራሷን የወረዳ ሰባት ነዋሪ እንደሆነች የገለፀች እንስትን ንግግር ሰማሁት ከአንዴም ሁለቴ፤ እንስቷ ግን በፓርቲ ፍቅር አቅሏን ስታ አዲስ ነገር ልትነግረን ቀርቶ ‹‹ለምን እዚህ መጥተው በጫካ አይፋለሙም›› ሁሉ ስትል ተደምጣለች፡፡ ስርዐቱ አሁንም የህዝብን ጥቄዎች ከማድመጥ ይልቅ የራሱን ሰዎች እንዲናገሩ እያደረገ የራሱን ድምፅ መልሶ እየሰማ ይገኛል፡፡ 


እዚህ ጋር ሁለት ነገሮችን ማየት ያስፈልጋል፡፡ አንደኛው ‹‹በሰለጠነ አገር በምቾትና በድሎት እየኖሩ ልጆቻችንን እሳት ውስጥ ለመማገድ›› የሚለው ሲሆን ሁለተኛው ‹‹ሰላማችንን ለማደፍረስ›› የሚል ነው፡፡ ይህ ተደጋግሞ እየተስተጋባ ያለ ነገር ነው፡፡ ከመጀመሪው ስጀምር በማንም ቀስቃሽነት አስተዋዋቂነት ሰልፍ ቢወጣ፤ ሰልፍ ወጪው አላማውን አምኖበትና ተቀብሎት እስከወጣ ድረስ ባለቤቱ ሰልፉን የሚያካሂደው ነው፡፡ ይህ ማለት ግን የሰልፉን እቅድ በውጭ የሚገኙ ሰዎች ማውጣት አለባቸው ማለት አይደልም፡፡ ይህን እንደየ አውዱ የመወሰን ስልጣን ያለው በቀጥታ በሰልፉ የሚሳተፈው ብቻ ነው፡፡ 
 
-
ባደባባይ ጭምር ባለማፈር የእነዚህን ዜጎች የመቀስቀስና የማስተዋወቅ ሚና የሚወጡትን የተለያየ ስም እየሰጡ እርግማን የሚያወርዱባቸው ዋነኛውን የመንግስትን ህገ አራዊት ተግባር ለመሸፈን ይመስላል፡፡ ዜጎች ሰላማዊ ሰልፍ ሳያስፈቅዱ (ማስፈቀድ የሚል ነገር ካለም ማለቴ ነው) በመውጣታቸው ብቻ ሰላምን በማስከበር ስም የዜጎችን ሞት ግን በምንም መንገድ ትክክል አያደርገውም፡፡ የስርዐቱ ሎሌዎች አለቆቻቸው የሚሉትን እያስተጋቡ ያሉትን ጨምሮ አነብናቢ ሚድያዎች እንዲሁም ይህን ባለማወቅ የሚደግሙ ሰዎች ስርዐቱ በንፁሃን ላይ የሚወስደውን ሞት፣ እንግልትና እስር ትክክል ነው እያሉ ነው፡፡ይህ የቱንም አይነት ምክንያት ቢቀርብ ትክክል አያደርገውም፡፡ ለገዢዎቹም ጊዜ ከመግዛት በቀር የሚያመጣው ነገር የለም፡፡ ለአገራችን ግን መጥፎ ባህል በመትከል ኢትዮጵያን የአንባገነኖች ቤተ ሙከራ የሚያደርግ ነው፡፡



ወደ ሁለተኛው ስመጣ ሰላም የሚለው ነው፡፡ ይህን ፅሁፍ እየፃፍኩ በቴሌቭዢን መስኮት ቀርበው ግለሰቦች አስተያየት እየሰጡ ነበር፡፡ ‹‹ህዝቡ ሰላም ወዳድ መሆኑን አሳይቷል፡፡›› ከሚሉት እንቶ ፈንቶዎች ጀምሮ የተለመደው ሰላማችንን ለማደፍረስ የሚለው በተለያየ መንገድ ተደጋግሞ የሚስተጋባ ነው፡፡ ለነዚህ ሰዎችና ላዘዟቸው ገዢዎች ጦርነት ባለመኖሩ ብቻ ሰላም አለ ማለት ነው፡፡ ኃይለኞቹ ገዢዎች ደካሞችን አስገብረው፣በጉልበታቸው የሰውን ልጅ መንፈስ ገድለው፣አእምሮው ታዛዥና ተገዢ ብቻ እንዲሆን አድርገው በድኑን አንደአሻንጉሊት በሚጫወቱበት ሁኔታ ሰላም አለ ይላሉ፡፡ 


‹‹አንድ ህዝብ በፖሊስና በጦር ሃይል ተሰንጎ ተይዞ ጭጭ ብሎ በደሉንና ጥቃቱን ቢችል ሰላም ነው ማለት አይደለም፡፡ ኃይለኛ ደካማውን ሲያጠቃ ሰላም የለም፤ብዙዎች ጥቂቶችን ሲያጠቁ ሰላም የለም፤ጥቂቶች ተደራጅተውና ታጥቀው ብዙዎችን ሲያጠቁ ሰላም የለም፡፡ ጸጥ፣ለጥ ብሎ መገዛት ሰላም አይደልም፡፡›› ጸጥ፣ ለጥ ብሎ መገዛት ሰላም የሚመስላቸውና ይህን ድንቁርናቸውን ለሌላው የሚግቱ ሰዎች ነገን እያበላሹ እንደሆነ አልገባቸውም፡፡