Wednesday, 22 February 2017

ሰላም፡ አንድነት፡ ተስፋ (ሰማያዊ)


ሰማያዊን አስመልክቶ  ፓርቲው እንደፈረሰ እንዲሁም አዲሶቹ ተመራጮች ላይ በተለይም አዲሱን ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ ላይ አሮጌው ፍረጃ እየወረደ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በተቃውሞ ጎራው ጉዳይ ላይ ደጋግሜ እንዳልኩት ፈረጃ ስልጡኑን ቁጭ ብሎ የመነጋገር እድልን የሚዘጋ አሮጌ መንገድ ነው፡፡ ይህም የተቃውሞ ጎራውን አንካሳ ሲያረግ የኖረ ነው፡፡ ላንዳንዶች ፓርቲ የግለሰቦች ንብረት ይመስላቸዋል፡፡ ለዚህ ነው ግለሰቦቹ ሲሄዱ የሚፈርስ እነሱ እስካሉ የሚቆም የሚመስላቸው፡፡ ለምሳሌ ኢ/ር ይልቃል የነበረውን ችግር ለመፍታት እድሉ በእጁ ነበር፡፡ ሌላው ሁሉ ቀርቶ በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ተሳትፎ መሟገት ይችል ነበር፡፡ በእጁ የነበሩትን መድረኮች ከመጠቀም ይልቅ ዳር ዳር ሲል ቆይቶ በመጨረሻ አማራጭ ያደረገው አሮጌውን መንገድ ነው፡፡ በግለሰቡ ፍቅር የወደቁ ተከታዮቹም ከዛ የተሻለ ነገር ማድረግ አልቻሉም፡፡


በጣም የሚገርመው  በማንኛውም ተቋማት ውስጥ በመሪነት ላይ ያሉ ሰዎች ጥሩ ነገር ሲሰራ መመስገናቸው ያለ በተቃራኒው ሲሆን ደግሞ ተጠያቂ የሚሆኑበት ሁኔታ ያለ ቢሆንም በኢትዮጵያ የተቃውሞ ጎራ ውስጥ ግን ለሚሰሩ ስህተቶች ሌሎችን ‹‹ወያኔ›› ማለት እራስን ከስህተት ነፃ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህን ሳይመረምሩ አሁንም ላለፉት ሁለት አስርታት በተሄደበት መንገድ ለመሄድ መጣደፍ ሌሎች ሁለት አስርታትን ቁጭ ብሎ ከመቁጠር የዘለለ ነገር አያመጣም፡፡ ለግለሰቦች ከማልቀስ በዘለለ ፓርቲዎች የለውጥ እንቅስቃሴውን መሸከም የሚያስችል አቅም እንዲፈጥሩ ከማገዝ ይልቅ የሥነ-ሥርዓት ኮሚቴው ላይ እንደሆነው የበላይ አመራሮችን የመጠየቅ አቅም መፍጠሩ ከማስመስገን ይልቅ የአሮጌው ፖለቲካ ሰለባ ነው ያደረገው፡፡ በዚህ ሁኔታ እንዴት ተቋማዊ ቅርፅ ያለው የለውጥ ሀይል እንደሚፈጠር ግራ ያጋባል፡፡



ሌላው አንድነት ላይ የሆነውን በማንሳት የሰማያዊም ተመሳሳይ እንደሆነ ለመግለፅ የሚሞከረው ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት እራስን ከስህተት ነፃ ለማድረግ እንዲሁም ካፈርኩ አይመልሰኝ ነው፡፡ ሌላው ሁሉ ቀርቶ አንድነት ውስጥ ከተፈጠረው ችግር ጀምሮ አባላት ከፅህፈት ቤታቸው በፖሊስ ሃይል እንዲወጡ ተደርጎ  ለአቶ ትዕግስቱ አይነት መካሪ አልባ ሰው ፓርቲው እስኪሰጥ አብሮት የነበረው ከፍ ካለው የፓርቲው መዋቅር  አንድ ግለሰብ ብቻ ነው፤ አባል የነበሩት በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ ሌሎች ከየት እንደመጡ እንኳን አይታወቅም፡፡ በሰማያዊ ውስጥ በብቸኝነት በሚመስል መልኩ አቶ የሺዋስ ላይ ፍረጃ የሚያካሂዱት እንደ አቶ ትዕግስቱ ከምርጫ ቦርድ ሰማያዊን በችሮታ ያገኘ ለማስመሰል ነው፡፡ ለዚህ ነው በጠቅላላ ጉባኤ ስለተሳተፉ ግለሰቦች፣ስለብሔራዊ ምክር ቤት አባላት፣እንዲሁም አሁን ስላሉት ስራ አስፈፃሚ አባላት ትንፍሽ ሲሉ የማይሰማው፡፡ ይህ የአሮጌው ፖለቲካ ሌላው ምሳሌ ነው፡፡



ከላይ እንዳልኩት ይህ አሮጌ ፖለቲካ ውዥንብር በመፍጠሩ ሰማያዊን አንካሳ ሊያደረግ እንደሚሞክር ግልፅ ነው፡፡ አሁን ያለው አመራር ለዚህ ጆሮ ሳይሰጥ ቆፍጠን ብሎ ጥሩ የሚባሉትን በማጎልበት ያለፉትን ህፀፆች በመመርመር ለምሳሌ በውስጠ ዲሞክራሲ እና በተቋማዊነት ላይ ጠንክሮ መስራት ይጠበቅበታል፡፡ ባጠቃላይ  የተቃውሞ ፖለቲካውን የአሮጌው ፖለቲካ መፈንጫ ከመሆን ለመታደግ መስራት የሁሉም የለውጥ ሀይል ድርሻ ነው፡፡

የትም የማያደርሰው አሮጌው ፖለቲካ…


ሰማያዊን አስመልክቶ ከዚህ ቀደም ያሉበትን ክፍተቶች አርሞ ወደፊት እንዲጓዝ በማሰብ የተወሰነ ነገር ብያለሁ፡፡ ይህንን ሳደርግ እንዲሁ በቀቢፀ ተስፈኛነት ሳይሆን ይህንን ማድርግ የሚያስችል አቅም በሰማያዊ ውስጥ አለ ከሚል ነው፡፡ ነገር ግን  እንዳየነው ችግሮቹ እንዳይፈቱ ጋሬጣ ከሆኑ አጥሮች ተሻግሮ መስራት አልተቻለም፡፡ ፖለቲካውን የከበቡት አካላትም ችግሮቹን ለመመልከትና የመፍትሄው አካል ከመሆን ይልቅ ትላንት በተሄደበት መንገድ ለመሄድ ያንኑ የመረጡ ይመስላል፡፡ ፍላጎታችን የተቃውሞ ጎራው በተለያየ ፓርቲ ስም የመቃወም እና የመቃወም ተግባሩን ብቻ እንዲቀጥል ከሆነ ይህ ተግባር በቂ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ መንገድ ግን የተቃውሞ ጎራውን መንግስት ለመሆን አያስችለውም፡፡ የፓርቲ ፖለቲካ ትግል ስልጣን ለመያዝ ነው፡፡ ይህ ገዢዎች እና አንዳንዶች ለራሳቸው ሲሉ ጠበብ አድርገው  እንደሚተረጉሙት የስልጣን ጥማት ሳይሆን ያሉትን ፕሮግራሞችና ፖሊሲዎች ለማስፈፀም ስልጣን መሳሪያ ስለሆነ ነው፡፡ነገር ግን ወደ ፓርቲ የሚመጡት በሙሉ ከላይ ያለውን ታሳቢ አድርገው ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ 


ፍላጎታችን የተቃውሞ ጎራ መንግስት የመሆን አቅም እንዲፈጥር ከሆነ ትላንት የሄድንባቸውን ብቻም ሳይሆን ዛሬም እየሄድንባቸው ያሉትን መመልከት መቻል አለብን፡፡ ከዚህ ቀደም ፅሁፌ ሰማያዊ የሚያደርገው ጠቅላላ ጉባኤ ፈተናቹን አልፎ ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚሸጋገርበት መሆን እንዳለበት አሳስቤያለሁ፡፡ ነገር ግን ይህን በውሃ ቀጠነ አንዳይሳካ ሲጥሩ ተመልክተናል፡፡ ቅንነቱ ብቻም ሳይሆን ለተቋማዊነት የመገዛት አቅሙ ካለ መተባበር እንጂ ፖለቲካውን አድሮ ቃሪያ ያደረገውን አሮጌ ፖለቲካ ተደግፎ ለማምለጥ ዝምታን መምረጥ ከዛም ሁኔታው ወደፊት ገፍቶ መሄዱ ሲታወቅ ‹‹ጠቅላላ ጉባኤው እየተካሄደ ያለው ምንጩ ባልታወቀ ገንዘብ ነው›› ማለት ከዛም አልፎ አዲስ መሪ ሲሾም ‹‹የፓርቲው ደንብ ተጥሷል›› ብሎ ማልቀስ መልስ ሳይሆን በግልፅ ቋንቋ ካፈርኩ አይመልሰኝ ነው፡፡


ለምሳሌ የኢ/ር ይልቃል ካቢኔ በቁጥር እንኳ ያልተሟላ መሆኑ ብቻም ሳይሆን እንደ ባህር ዳሩ ሰልፍ አይነት ውሳኔዎችን በደፈናው ወስኖ ከተቁዋማዊነት ውጪ በሆነ መንገድ ሰልፉ ሊካሄድ ከአስራ ሁለት ሰአታት በታች በቀሩበት ሁኔታ ያስተባበለበት መንገድ የአመራሩን ድክመት በግላጭ ያሳየ ነው፡፡ ከተጠያቂነት አንፃር የተካሄደው ቸልተኝነት ለምሳሌ ያክል የሥነ-ሥርዓት ኮሚቴውን ውሳኔ የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን አግዶ ያቆየበት መንገድ፤ እንደገባኝ በብዙ ተፅእኖም ውስጥ ሆኖ  ነገሩን በቅንነት ለማየት ከመሞከር ይመስለኛል ቢሆንም ፓርቲውን ወደፊት ሊያራምድ አልቻለም፡፡ ይባሱኑ  ብዙ የፓርቲ አባላቶችን  አስከፍቶ ከፓርቲው እንዲሸሹ ምክንያት ሆኗል፡፡



 ኢ/ር ይልቃል ከአዲስ አድማስ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ ሳነብ  በስም እየጠቀሰ እነዚህን የመሰሉ የፓርቲው አባሎች የመባረር ውሳኔ ተላልፎባቸዋል ይልና ‹‹ታዲያ እነዚህን ሁሉ አመራሮች የሚያባርር አካል፣አላማው ምንድን ነው? ይሄ ሆን ብሎ ፓርቲውን ለማፍረስ የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው፡፡›› በኢ/ር ይልቃል አገላለፅ የጠቀሷቸው ግለሰቦች ድርጅት/ፓርቲ ሆነዋል ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው ቀድሞውኑ ፓርቲው ያስቀመጠውን መንገድ መከተል ያልፈለጉት፡፡ ይህ ደግሞ ለተቋማዊነት አለመገዛትም ነው፡፡ የፓርቲው የስነ-ስርዓት ኮሚቴ የበላይ አመራሮችን የመጠየቅ አቅም መፍጠሩ ከማስመስገን ይልቅ የአሮጌው ፖለቲካ ሰለባ ነው የሆነው፡፡ ኢ/ር ይልቃልም በዘወርዋራ ያለው አዲስ ሳይሆን አሮጌው የፍረጃ ፖለቲካ ነው፡፡ ይህን አሮጌ የፍረጃ ፖለቲካ እንዲቀጥል የሚያግዙ ሰዎችም የሚያቀርቡት የሞተ አመክንዮም መሬት ላይ ያለውን እውነታ የሚያንፀባርቅ ሳይሆን ይህንኑ አሮጌ ፖለቲካ የተደገፈ ነው፡፡ የሚሰሙ ከሆነ የትኛውም የፓርቲ አባል ጠያቂ መሆኑ የሚደገፍ ቢሆንም ጠያቂ ስለሆነ ተብሎ የማይነካና የማይጠየቅበት ምክንያት የለም፡፡



ፓርቲው በሰኔ ወር 2007 ዓ.ም ሁለተኛውን ጠቅላላ ጉባኤ ካደረገ በኋላ በፖለቲካው በኩል ምንም የጎላ እንቅስቃሴ አላደረገም፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ችግሮች መኖራቸው የሚታወቅ እንደመሆኑ መጠን በአመራሩ ይህ እንዲፈታ አባላት ተጠርተው እንኳን ውይይት አልተደረገም፡፡ ይህ ሁሉ ባለበት ሁኔታ ፓርቲው ለጠቅላላ ጉባኤ በሚዘጋጅበት ወቅት ለዚህ አጋዥ ሆኖ ከመሰለፍ ይልቅ ሁኔታውን  ችላ በማለት ከዚህ ፅሁፍ ጋር ተያይዞ የቀረበው ምስል እንደሚያሳየው  መስከረም 24 2009 ዓ.ም ሃምሳ የማይሞሉ የፓርቲው አባላት ባሉት በወቅታዊ ጉዳዮችና በፓርቲው የወደፊት የስራ እንቅስቃሴ ዙሪያ ከአባላት ጋር ውይይት ተካሄደ፤ የሚል ዜና ተሰራ፡፡ በፓርቲው  ውስጥ ያለው ችግር እንዲስተካከል ሳይጥሩ  በምስሉ እንደሚታየው ከተሰብሳቢዎቹ መጀመሪያ ላይ ያለው አቶ ስለሺ ፈይሳ እና መሰሎቹ  በአዲሱ አመራር  በቅርቡ በፓርቲው ፅ/ቤት ሊካሄድ በታቀደው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በመገኘት ህጋዊ ሊቀመንበሩ ኢ/ር ይልቃል ነው፤እናንተ ህገ-ወጦች ናችሁ በማለት ወደ ግብግብ ያመሩበት ሁኔታ ከግለሰብ ፍቅር ውጪ ሌላ ነው ብዬ ማሰብ ይቸግረኛል፡፡ ይህ ደግሞ የትም አያደርስም፡፡


አንዳንዶች በግርድፉ የሰማያዊን ሁኔታ ከአንድነት ጋር አንድ ሊያደርጉት ይሞክራሉ፡፡ አንድነት ውስጥ የሆነው ከዚህ በጣም የተለየ ነው፡፡ ይህን መረዳት የሚፈልግ መለስ ብሎ ማየት ይኖርበታል፡፡ እዚህ ጋር ግን መርሳት የሌለብን ግለሰቦች በተለይም በአመራር ደረጃ ያሉ ሰዎች በሚፈፅሙት ስህተት የሚፈጠሩትን ችግሮች እስከመቼ በፍረጃ እና በገዢዎቹ እያሳበብንና ስህተቱን የሰሩትን ነፃ እያደረግን እንቀጥላለን? ይህ ለተቃውሞ ጎራው የስህተት መደበቂያ አይሆንም ወይ? እዚህ አገር በተለይ ፓርቲዎች ከመቋቋም ጀምሮ በገዚዎች ተፅእኖ እንደሚደርስባቸው እሙን ነው፡፡ ይህ ከሆነ ለዚህ መሻገሪያን መንገድ ማዘጋጀት የእነሱ ተግባር አይደለም ወይ? ለዚህም ሃላፊነቱን መውሰድ የለባቸውም ወይ? ይህን ሳንመልስና አለባብሰን አሮጌውን ፖለቲካ መከተል የትም የማያደርስ ብቻም ሳይሆን አንድ እግር ወደፊት አንድ እግር ወደኋላ አይነት ነው፡፡


አሁን የፓርቲው ሊቀመንበር ሆኖ የተመረጠው አቶ የሺዋስ ከኢ/ር ይልቃል ጋር ከአንድነት ‹‹መርህ ይከበር›› ብሎ የወጣ ብቻም ሳይሆን የብሔራዊ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ሆኖ ሲሰራ የቆየ ነው፡፡ በዚህም ጊዜ ለእስር ተዳርጎ ሁለት አመታት ለሚጠጋ ጊዜ በእስር የቆየ ነው፡፡ አሁን በአፍራሽነት የሚፈረጀው እሱ ብቻ ሳይሆን ሰማያዊ ተቋማዊ ቁመና ያለው የለውጥ ሀይል ሆኖ እንዲወጣ ደፋ ቀና ያሉትም ጭምር ናቸው፡፡ የተቃውሞ ጎራው ተዋናዮች ከትላንት ስህተት ከመማር ይልቅ ዛሬም በአሮጌው መንገድ ለመትመም የሚጣደፉ ነው የሚመስለው፤ አሁን አሁን እንደምናየው የፓርቲ አባላት ወደ ፓርቲ ሲመጡ ስርዐቱን ከመጥላት በዘለለ፤ ርዕዮተ አለም፣ ተቋማዊነት እና በውስጠ ፓርቲ ዲሞክራሲ  ከመሳብ ይልቅ በግለሰቦች ፍቅር ወድቀው ነው አባል የሚሆኑ የሚመስለው፤ ከዚህ አኳያ እነዚህ ሰዎች ሌላው ሁሉ ቀርቶ በምክንያት ክርክር ያደርጋሉ ብሎ ማሰብ ያስቸግራል፡፡ ከዚህ አኳያ የተቃውሞውን ጎራ ከጅምሩ የምክንያት ሜዳ ከማድረግ ይልቅ የአሮጌው ፖለቲካ መፈንጫ ሆኗል፡፡ ይህ ሳይዘምን እና ሳይስተካከል መንግስት መሆን አቅም ይፈጠራል ማለት ዘበት ነው፡፡