አሁን
ለምንገኝበት ውጥንቅ እና ነገም ለሚከሰተው ችግር መሰረቱ በዘመኑ የነገሰው ቅጥ ያጣ ስንፍናችን ነው፡፡ በጣም የሚገርመውና የሚያሳዝነው ለስንፍናችን የምንሰጠው የሽፋን ስም እንዲሁ ስንፍናችንን ለመደበቅ እንደሆነ ያስታውቃል፡፡ ምክንያቱም ስንፍናችንን ማመን አንፈልግም ለዛ ነው፡፡ ስለማናምን ለዚህ የሺፋን ስም እናወጥለታለን፡፡ በዛ ሽፋን ስም ተከልለን የቁቁለት ጉዟችንን እናፋጥናለን እንጂ ቅንጣት ታህል ፈቀቅ አንልም፡፡ ለዚህ ደግሞ ሪፍረንስ የሚሆኑ አባባሎችም አናጣም…
ይህ
የስንፍናችን ጥግ ሄዶ ሄዶ በምናብ እንድንኖር እያደረገን ያለ ይመስለኛል፡፡ ይህ ባይሆንማ መሬቱ ይህን ያህል አይረቀንም ነበር፤ ከምንናወራቸው ብዙ ሺ ቃላት በጣት የሚቆጠሩትን መሬት ማውረድ ሰማይን የመንካት ያህል እሩቅ አይሆንብንም ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ያላረስነውን ለማጨድ የምንኳትን እኮ ነን! መጠጥና ሲጋራ ላይ በየቀኑ ኢንቨስት እያደረግን ነገር ግን ለተቋማት ሲሆን ንፉግ የምንሆን፤ ነገር ግን ነፃ ተቋማት እንዲኖሩን የምንመኝ የህልም አለም ሰዎች…
ስንፍናችንን በሐይማኖት ውስጥ ደብቀን፤ መሬት ላይ ያለውን ችግር አውቀን ተረድተን ወደ መፍትሄው ለመሄድ ጉልበታችን ሽብርክ ሲል ያችው የማምለጫ ቃላትን በማምጣት ቅጥ ላጣው ስንፍናችን የዳቦ ስም የምናወጣ… እዚህ ላይ እንደው በዝች አገር ያለው ችግር ከቅጥ አልፎ የግፍ ፅዋውም ሞልቶ ፈሶ የስርዐት ለውጥ ቢመጣ እነዛን ተቋማት ማን ሊቀይርልን ነው? ይህ ምን የሚያስጨንቀን ሆነና… ዛሬም እግርና እጃችንን አጣጥፈን በመቀመጥ ነፃ አውጪ የምንጠብቅ የተስፋ አለም ሰዎች እኮ ነን…
በምንሰራበት ቦታ እንኳ ኢ-ፍትሃዊነትን፣አምባገነንነትን ወ.ዘ.ተ ከመቃወምና ይህም እንዲሻሻል የድርሻችንን ከማድርግ ይልቅ ‹‹መኖር እፈልጋለሁ›› በምንላት የስንፍና ቃላችን ተደብቀን ሌሎችን በዚህ መንገድ እንዲሄዱ በማድረግ ማጎንበስ እንዲማሩ ዱላ እናቀብላለን፡፡ ከዚህ ተሻግረው የድርሻቸውን ለማድረግ የሚጣጣሩትን ከማበረታታት ይልቅ ያችኑ የስንፍና ዱላችንን ይዘን ቀና ቀና ማለት የጀመሩትን አናት አናታቸውን በመምታት እንደራሳችን እንዲያጎነብሱ እናደርጋቸዋለን፡፡ የእኛ ማጎንበስ ሳያስጨንቀን የሌሎች ቀና ማለት እረፍት ይነሳናል፡፡
ድክመታችንንና ስንፋናችንን ስፋት ለመደበቅ ሲባል ብቻ ይህንን ቀንቋ፣ይህንን ሐይማኖት እንወክላለን እያለን አለም የአንድ መንድር ያህል በሆነችበት ሁኔታ እኛ ግን አሁንም የመኖር ዋስትኛችን ልዩነትን መንዛት አድርገን ይኸው አለን… በሐይማኖት ተቧድነን ፣በቋንቋ ተቧድነን ከዛም ዝቅ ሲል በወንዝ ተሰባስበን፣ ይህ ሁሉን የእኛ ዲግሪ መጫን፣ማስተርስ መያዝ ከዛም ከፍ ማለት ከአጥራችን እንኳን መሻገር ሳያስችለን ይኸው አጥራችንን ውስጥ ሆነን በእኔ ምን አገባኝ ስሜት የሌላው ስቃይና ህመም አልሰማን ያለን ከእንቅልፋችን ብዛት የነገ ተረኞች እንደሆንን እንኳ የረሳን…
የውሸት ጣራ የውሸት ግድግዳ ገንብተን ባጠቃላይ ህይወታችን የውሸት ሆኖ ሌሎች እውነትን እንዲፈርዱ የምንፈልግ ህልመኞች እኮ ነን… አሁን ያሉትን ችግሮችን እራሳችን ለመመፍታት ሳንችል የሚቀጥለው ትውልድ ይፈተዋል እያልን የምንቀልድ ጉደኞች እኮ ነን… አግብተን ለመውለድ የምንጣደፈውን አቤ ጉበኛ ‹‹እልወለድም›› ባለው ድርሰት ውስጥ አይነት ሰው በሽል ውስጥ ቢኖር ምን ይውጠን ይሆን? አዎ አሁን ባለው ስንፍናቸውን እንዲሁ ወደዚህ ምድር የምናመጣቸው ልጆች ይህን የሚመስል ሁኔታ አዘጋጅተን መሆኑን ቢያውቁ ኑሮ ምን ይሉን ይሆን?
የዘመናት ቁጭታችንና ስቃያችን መነሻ የአባይን ግድብ አለመገደብ የሚመስለን ይህም ግድቡ ተገንብቶ እንዳለቀ ችግሮቻችን በሙሉ በአንድ ሌሊት ድራሻቸው የሚጠፋ የሚመስለን ነገር ግን በተግባር ቁልቁለታችንን ያፋጠኑትን አሁንም ስልጣንን መግራት አለመቻልን መሆኑን እረስተን በአንባገነኖች መዳፍ ስር እየተጎሳቆልን እንገኛለን፡፡ እድገት ማለት ህንፃ ወደ ላይ መውጣት አስፋልት መነጠፉ የሚመስለን ነገር ግን ሰዋዊ ልማቱ የት ደረሰ ብለን የማንጠይቅ…
እራስ
ወዳድነታችን ጣራ ላይ ወጥቶ እኔ እኔ ማለት አብዝተን የአንዳችን መኖር የሌላችንም መኖር መሆኑን እንኳን የረሳን ሰነፎች… ሌሎች በቀደዱልን ለመፍሰስ የማናወላውል… ባጠቃላይ ተመቻችተን ከተኛንበት የስንፍና ዋሻችን ላለመውጣት የተገዘትን ይመስል ከዋሻው ውስጥ ሆነን እንኳን ከዚህ የወጡትን ሰዎች በሚናገሩት የምንደነብር፣ጥረታቸውን በለመድናት የስንፋና ቃላችን የምናጣጥል፡፡ ከዚህም አልፎ የስንፍናችን ጥግ የት ይደረስ ይሆን? ከስንፍናችንስ ጋር ተስማምተን እስከመቼ እንዘልቅ ይሆን? በዚህ ሁሉ መሃል ምጣችንስ ምን ያህል ይረዝም ይሆን?