Wednesday, 20 May 2015

ስርዓቱ የትኛውን በር ነው የሚፈልገው?



እየሆነ ያለው ሁኔታ እጅግ ስሜትን የሚፈታተን ነው፡፡ በነጋ በመሸ ቁጥር የምንሰማው የንፁሃኖቻችንን እስር፣እንግልትና መዋከብ ሆኗል፡፡ የአንድነት ፓርቲ አባላትና አመራሮች ይህን ስርዐት ከእነ እንከኑ የወንድ በር በመስጠት ፖለቲካው አዲስ መልክ እንዲይዝ እንዳልታገሉ ይህ ከፋፋይና አምባገነን ስርዐት ግን ፓርቲውን ማፍረሱ ሳያንስ አባላቱን ማሰሩን፣አገር ጥለው እንዲሄዱ ተፅእኖ ማሳደሩን፣ማዋከብና ማስፈራራት ስራዬ ብሎ ይዞታል፡፡

ይህን ቧልተኛ ምርጫን ተከትሎ የዛፍ ላይ እንቅልፍን የተያያዘው ከፋፋዩ ስርዐት ኮሽ ባለ ቁጥር ንፁሃኑን አስቀያሚ ወደ ሆኑ ማጎሪያዎቹ መውሰዱን ተያይዞታል፡፡ በአረና ፓርቲ እንዲሁም በሰማያዊ ፓርቲ አባላት ላይ እያደረሰ ያለው እስርና ወከባ ስርዐቱ በምንም ሁኔታ በህግ ለመገዛት ቁርጠኝነት እንደሌለው አሳይቷል፡፡ ምርጫ፣መድብለ ፓርቲ እና ዲሞክራሲ የሚላቸው ነገሮች በንድፈ ሃሳብ እንጂ በተግባር እንዲወርዱ እንደማይፈልግ አሳይቷል፡፡
 
በንፁሃን ደም ለተጨማለቀ ስርዐት ሰላማዊ ትግል የወንድ በር ነበር፡፡ ግና ይህንን ሊያደርጉ ቀና ደፋ የሚሉትን ጎበዛዝት እና ወይዛዝርት ስም እየሰጠ ወደ ማጎሪያው መውሰዱን ተያይዞታል፡፡ ያለፈውን ሁኔታ በመገምገም ለአገራችን የሚጠቅማት ሰለማዊ ትግል ነው ብለው የሚያምኑትን የእድሜ እኩዮቼን ከዚህ መንገድ እንዲወጡ እየተጋ ነው፡፡ ነጋ ጠባ ንፁሃኖቻችንን ወደ ማጎሪያው እያወረደ -ሰብአዊ ድርጊት በመፈፀም እንዲሁም ‹‹ሰላማዊ ትግል እንደማይሰራ በመንገር ወንድ ከሆናችሁ ለምን ብረት አታነሱም›› በማለት ላይ ይገኛል፡፡

 
ስርዐቱ ሰላማዊ ትግል የመረጡ ሃይሎች ከሌላው ያነሰ ወኔ ስላላቸው ይመስለዋል፡፡ እውነት ለመናገር ጦርነት ላለፉት ብዙ አመታት ያየነው ነው፡፡ ይህንን ገምግመው የወደፊቱ የተሻለ የሚሆነው በሰላላማዊ ትግል እንደሆነ በማመን ነወ የሰላም ትግልን የመረጡት፡፡ ለአገራችንም የሚጠቅማት ይህ ነው፡፡ በተለይ የስርዐት ለውጥ ብቻም ሳይሆን የተቋማት ለውጥ እንዲመጣ የምንሻ ዜጎች ይህን መስመር የምንደግፈው ለዚሁ ነው፡፡ ስርዐቱ ግን ይህን ከወኔ ማነስና ከሌላ በመቁጠር በሚነዛው ፕሮፓጋንዳው የእድሜ እኩዮችን እየገፋቸው ይገኛል፡፡


‹‹የሰላም በሮች ሲዘጉ የአመፅ በሮች ይከፈታሉ›› ያለው ማን ነበር? አምባገነኖች ጊዜ አያስተምራቸውም፡፡ ከቀድሞ አምሳያቸው ውድቀት አይማሩም፡፡ ለዚህ ይመስላል የኛ አመባገነኖች እሩቅ እንኳን ሳይሄዱ ከደርግ መማርን ሳይችሉ አሁንም ንፁሃንን በማሰርና በማንገላታት የህዝብን የለውጥ ኃይል ማቆም የሚቻል ይመስላቸዋል፡፡ ደርግ ንፁሃኑን በጅምላ ቢጨፈጭፍ፣ቢያስር የህዝብን የለውጥ ሃይል መግታት አልተቻለውም፡፡ ከአፍሪካ የሚያስፈራ ሰራዊት ይዞ ነገሮችን መለወጥ አልተቻለውም፡፡ ዘመነኞቹ አምባገነኖች በመኮፈስ ቁልቁለታቸውን ተያይዘውታል፡፡


ብረት ባነሱት ላይ ቅሬታ የለኝም፡፡ ይህን እንዲመርጡ ስርዐቱ ከሚገባው በላይ እንደገፋቸው አውቃለሁ፡፡ የቀረነውን በፈለጉት ሰአትና ወቅት ሊያስሩ ይችለሉ፡፡ ሰላማዊ ትግልን መርጠን የምንታሰረው ከሌላው ያነሰ ሞራል ስላለን ሳይሆን የተነሳንለት አላማ ስለሚያስገድደን ነው፡፡ ወንድም ወንድሙን የሚገልበት ሁኔታ መቆም አለበት፡፡ እስካሁን ሲደረግ የነበረው ጥረት የስርዐት ለውጥ እንዲመጣ ብቻም ሳይሆን የተቋማትም ለውጥ እንዲመጣ ነው፡፡

 
በወንጀልና በሙስና ለተጨማለቀው ስርአት የተሰጡት እንድሎች እያለቁ ናቸው፡፡ የሊቢያው አምባገነን ሙሃመድ ጋዳፊ ተቃዋሚዎቻቸው ስርዐታቸውን ለመገርሰስ ጥቂት በቀራቸው ሁኔታ እንኳ ትእቢታቸው ሳይቀንስ ‹‹አይጦች›› ነበር ሲሏቸው የነበረው፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ግን እንደ አይጥ ከጉድጓድ እየተጎተቱ የወጡት ተቃዋሚዎቻቸው ሳይሆኑ እራሳቸው ናቸው፡፡ የአምባገነኖች ባህሪ ይህ ነው፡፡ ሊቢያ አሁን ያለችበት ሁኔታ ሁሉም የሚያውቀው ነው፡፡ አምባገነኖች እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል የሚሉ ናቸው፡፡ ሊቢያ አሁን የምትገኝበት ሁኔታ ለዚህ ምሳሌ ነው፡፡


የስርዐቱን ማጎሪያዎች ያጨናነቁት የሰላማዊ ትግል አቀንቃኞችም ይህንን መንገድ የመረጡት ከሌላው ያነሰ ወኔ ስላላቸው ሳይሆን የአገራቸው ሁኔታ ስለሚያሳስባቸው ነው፡፡ ግና ስርዐቱ የወንድ በሩን እምቢ ካለ ምን ይደረጋል፡፡ አምባገነኖች እንዲህ ናቸው፡፡ በሰላማዊ ትግል የወንድ በር ተሰጥቶት ያልወጣ፤ ከሰላም በር ይልቅ እንደ ጋዳፊ ከጉድጓድ እየተጎተተ እንዲወጣ የአመፅን በር ያመቻቻል፡፡ የኢህአዴግ ሰርአት እያደረገ ያለውም ይህኑ ነው!

No comments:

Post a Comment