Saturday, 4 July 2015

ነፃ አውጪና ነፃ ወጪ…?


በዚህ ፅሁፍ በተለይ ነፃ አውጪዎችን አስመልክቶ የምለው ለነሱ በተለይ ለተግባራቸው እውቅና ላለመስጠት ፈልጌ ሳይሆን እነዚህ ወገኖች አንድም በአገር ፍቅር ስሜት አንድም ዲሞክራሲንና መልካም አስተዳድርን በመናፈቅ ፋኖ ተሰማራ በማለት ብረት አንግበው በርካቶች ወድቀዋል፡፡ ነገር ግን በበርካቶች መስዋትነት ስልጣን ላይ የተቆናጠጡት መሪዎች እንደዛ አምርረው የሚጠሉትን ስርዐት ለመሆን ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡ ከያኒው ‹‹አዲስ ንጉስ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ›› እንዲል! ስለሆነም ይህ በተጨባጭ እንዴት ሊሆን እንደቻለና አሁንም እዛው ትርኩት ውስጥ የመሆናችን ሚስጥር ምን እንደሆነ ማየት ይሆናል፡፡


እንዴት ትላንት ያንን ሁላ መስዋትነት ተከፍሎ ዛሬም ወደ ቀድሞው መመለስ ተቻለ? አሁን በስልጣን ላይ ያሉት ሰዎችስ ትላንት አብረዋቸው የነበሩትን በተለይም በፍፁም ቀናኢነትና አገር ፍቅር ብለው የወደቁትን እረስተው ስልጣን ላይ ሲወጡ እንዴት የለየላቸው አማባገነኖች ሆኑ? ከዚህ በኋላ ለስንፍናችን የዳቦ ስም እያወጣን የምንቀጥልበት ምክንያት ያለ አይመስለኝም፡፡ ነፃ አውጪ ነን የሚሉ አካላት ያን ያህል አመት በትግል ሲጓዙ ነፃ ወጪው ህዝብ ምን ሲያደርግ ቆየ? እንደምናየው አሁንም ህዝቡ ነፃ አውጪ መጠበቁንና ወደ ሰማይ መመልከቱን አላቆምም፡፡


አንደሚገባኝ አሁን በስልጣን ላይ ያሉትን የአገራችን መሪዎች ጨምሮ በርካታ አምባገነኖች ሲፈጠሩ አምባገነን አልነበሩም፡፡ አሁን በስልጣን ላይ ያሉት ገዢዎችም ትላንት በለጋ እድሜያቸው ወደ ትግል ሲገቡ በውስጣቸው አሁን የያዙት መነፋፋትና ንቀት አልነበረም፡፡ በሂደት ግን ይህ እንዲፈጠር ምክንያት የሆኑት ነገሮች ምንድን ናቸው የሚለውን መመልከትና መለየት ነገ መፍጠር ለምንፈልገው ስርዐት አስፈላጊ ነው፡፡ ትላንት በቅንነትና በአገር ፍቅር ስሜት ተገፍተው ህይወታቸውን የሰዉ ዜጎች ለደቂቃ ቢነቁና ትላንት አብረዋቸው በረሃ የወረዱትን ጓዶቻቸው ቢመለከቱ ምንኛ ሊያዝኑ እንደሚችሉ መገመት ቀላል ነው፡፡


ያለፉትን ሁሉ ትተን ከደርጉ አምባገነን አገዛዝ ነፃ አወጣናችሁ የሚሉንን ዘመነኞቹ አምባገነኖች ብናይ እንኳ ከሁለት አስርታት በላይ በትጥቅ ትግል ተፈትነው አገር መምራት ሲጀምሩ ትንሽ መገዳደር የገጠማቸው ከተወሰኑ ተቋማት ነው፡፡ ያንንም መሳሪያ ተሸካሚዎቹ በማሰር በማስፈራራት አገር ጥለው እንደሰደዱ በማድረግ አከባቢውን ለአገዛዛቸው እንዲመች አድርገውታል፡፡ አሁንም ይህ ተግባራቸውን አጥብቀው እንደቀጠሉበት ነው፡፡ ይህ እንዳይሆን ምን መሰራት ነበረበት? በእርግጥም ዛሬም ሆነ ትላት ለአፍሪካ ነፃ አውጪዎች ሳይሆን ነፃ ተቋማት ናቸው የሚያስፈልጓት፡፡ እዚህ ላይ ፕሬዚደንት ኦባማ ለአፍሪካ ጠንካራ ግለሰቦች ሳይሆኑ ጠንካራ ተቋማት ናቸው የሚያስፈልጓት ያሉትን ልብ ይሏል፡፡


አሁንም እንደሚታየው የአገራችንን ችግር አንድ ፓርቲ እንዲፈታው መጠበቅና ትግሉ ከገዢዎች ጋር ብቻ የሚደረግ ትግል አድርጎ መመልከት ስህተት ነው፡፡ ትግሉ ከህዝቡ አስተሳሰብ ጋርም የሚደረግ እንደሆነ መረዳት እና የተግባር እንቅስቃሴ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ሁሉም ፖለቲከኛ ይሁን ባልልም ግን ሁሉም በየደረጃው የራሱን ሃላፊነት መወጣት መቻል አለበት፡፡ አንዱ ውድ ህይወቱን ጭምር ገብሮ ሌላው አብዛኛው ወጣትነቱን በእስር አሳልፎ ሌላው ደግሞ በዳንኪራና በጭፈራ እንዲሁም እኔ ምን አገባኝ በሚል ገዳይ አባባል እንዲሁም ጎመን በጤና በሚል የዳቦ ስም ተሸፍኖ ብንጓዝ ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት አንችልም፡፡


እንደትላንቱ አሁንም ጠንካራ ተቋማትን ሳንፈጥር በጥቂቶች መስዋትነት ስርዐት ቢቀየር የሚመጣው ስርዐት አምባገነን ላለመሆኑ ዋስትናችን ምንም ነው፡፡ ምክንያቱም ያንን ሊጠብቅልን የሚያስችል ተቋማትን አልፈጠርንምና! አንዳንዶች የፖለቲካ ድርጅቶችን ያለምንም መስዋትነት ሁሉንም አቡክተው እንዲጋግሩላቸው የሚፈልጉ አሉ፡፡ ይህ ስህተት ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተግባር ይህ አይደለም፡፡ ይህን ስል ግን የፖሊሲ ለውጥን ጨምሮ ሌሎች ለውጦች አይኖርም ማለቴ ሳይሆን ተቋማትን በተመለከተ ዋነኞቹ ባለድርሻ አካላት እነሱ ሳይሆኑ መላው ህዝብ ነው፡፡


አንዳንዴም ሳስበው የነፃ አውጪ ጉዳይ ስንፍናን የሚያስተምር መስሎ ይሰማኛል፡፡ ምክንያቱም እራሱን እንደ ባለድርሻ አካል ቆጥሮ በሚደረገው ትግል ላይ የኔነት ስሜት ካላሳደረ ነገም ሌሎች የስህተት መንገድ ቢከተሉ ተመለሱ ብሎ የሚከራከርበት ወኔ አኖረውም፡፡ በተግባር የለውጡ አካል ሆኖ ከነበረ ተመለስ ሲባል እያንገራገረ የሚመለስ ሳይሆን በትጋትና በንቃት የሚቆም ይሆን ነበር፡፡ የዝች አገር ጉዳይ የእያዳንዱ ዜጋ ጉዳይ እንጂ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳይ ብቻ አድርጎ መውሰድ የስህተቶች ሁላ አንጓ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡


ከላይ እንዳልኩት ሁሉም ፖለቲከኛ ይሁን የሚል እብደት ባይኖረኝም ለነፃና ጠንካራ ተቋማት ግንባታ ሁሉም አሻራውን ማሳረፍ መቻል ይኖርበታል፡፡ አሁንም ሃይማኖተኛውም፣ ምሁሩም ሌላውም ዜጋ የሆነ አካል መቶ ነፃ እንዲያወጣው የሚጠብቅ ከሆነ ጉዳዩን አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ የኢትዮጵያንም ጉዳይ አስቸጋሪ ያደረገው ይህ ይመስለኛል፡፡ ደግሞም እንበልና የሆነ አካል መጥቶ ነፃ አወጣው ነገ የያዘውን ነፃነት አስጠብቆ የሚያቆይ ጥንካሬና ንቃተ ህሊና ካልገነባ አሳልፎ የማይሰጥበት ምክንያት የለም፡፡ ይህም ነገሩን ዉሃ ቅዳ ውሃ መልስ ያደርገዋል፡፡


ከላይ ስለስንፍና አንስቻለሁ፤ ይህንም ህዝብ መስዋትነትን መክፈል እንዳለበትና በሂደትም ለትግሉ የባለቤትነት ስሜት መያዝ እንዳለበት ለመጠቆም ነው፡፡ ያ ካልሆነ ግን ለጥቂት ጊዜ መስዋት ከፍሎ ነፃነትን ከመጎናፀፍ ይልቅ ባርነትን የሚመርጥበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ እዚህ ላይ በግብፅ ለበርካታ አመታት በግፍ ሲሰቃዩ የነበሩ እስራኤላውያን በነፃ አውጪያቸው ሙሴ/ሙሳ ታግዘው የነፃነቱን ጉዞ ይጀምራሉ፡፡ በሂደትም ፈታኝ ሁኔታዎች ሲገጥማቸው እንዲህ ነበር ያሉት ‹‹ምነው በግብፅ ሳለን እግዚአብሔር በገደለን ኑሮ፤በዚያ ሌላው ቢቀር ስጋም ሆነ ምግብ የፈለግነውን ያህል መመገብ እንችል ነበር፤እናንተ ግን ሁላችንም በራብ እንድናልቅ ወደ እዚህ በረሃ አመጣችሁን ‹‹ ሲሉ አማረዋል፡፡ በጉዟቸው የገጠማቸውን ጥቂት መስዋትነት ከመቋቋምና ነፃነታቸውን ከመጎናፀፍ ይልቅ ለበርካታ አመታት የታከታቸውን የሰቆቃና የባርነት ህይወት ናፈቁ፡፡


በአገራችንም ‹‹ከማያውቁት መልዐክ ይልቅ የሚያውቁት ሰይጣን ይሻላል›› የምትል ጭቆና አርዛሚ አባባል አለች፡፡ እስራኤላውያኑም በሙሴ መሪነት በሚያደርጉት ጉዞ በደረሰባቸው ፈተና ከማያውቁት የነፃነት ህይወት ይልቅ የለመዷት የባርነት ህይወትን መመኘታቸውና እኛም ከማናውቀው ነገር ግን አዲስ ነገር ይዞ ከሚመጣው ሃይል ይልቅ እያሰረን፣እያሰደደን፣ እየገደለን ያለውን ከፋፋይ ስርዐት የሙጥኝ የማለታችን ሚስጥሩ ምንድን ነው ካልን? ስንፍናን ባህል ማድረጋችን ነው፡፡ ለኔ ከዚህ የተሻለ ትርጉም ለጊዜው አላገኘሁለትም፡፡ ይህ ድምበሩን ሲሻገር ማህበራዊ ቀውስ ማስከተሉ አይቀሬ ነው፡፡ ስለሆነም ዛሬ በደንታቢስነት እኔ ምን አገባኝ እንዲሁም ለፍርሃታችን የዳቦ ስም በማውጣት የምንቀጥልበት ሁኔታ ላይኖር ይችላል፡፡


የሆነው ሆኖ አሁንም ነፃ አውጪና ነፃ ወጪ የሚሉ ትርክቶች የኢትዮጵያን የፖለቲካ መድረክ አንደተቆናጠጡ ነው፡፡ አሁን በተግባር እንደምናየው ግን እያንዳንዱ ግለሰብ በተሰማራበት ነፃና ጠንካራ ተቋምን ከመፍጠር ይልቅ በፍርሃት ተሸብቦ፤ ስንፍናውን ፊት ለፊት ከመጋፈጥ ይልቅ ለስንፍናው የዳቦ ስም እያወጣ በመቀጠል የዝች አገር ችግር ከሌሎች የተለየ እንደሆነ በማሰብ፤ ይህም የሚፈታው አንድም ባለፈው ተሞክሮ ባልሰመረውና የምንጠብቀውን አይነት ለውጥ ባላጎናፀፈን መንገድ መሆኑን መተረክ ሲሆን ሁለተኛው ከጊዜ ወደ ጊዜ በስልጣን ላይ ያሉት ከፋፋይና አምባገነን ገዢዎች የሚፈፅሙትን ተግባር ያለቅጥ አግዝፎ በማየት ከነጭራሹ በምድራዊ ሀይል መለወጥ እንደማይቻል በማሰብ ወደ ላይ ማማተር ነው፡፡


እነዚህ ግን ለህመማችን ጊዜያዊ እንክብሎች ናቸው፡፡ በእርግጠኝነት ለመናገር ከዚህ አስተሳሰብ መውጣት ካልቻልን የስርዐት ለውጥ እንጂ የተቋማት ለውጥን ማምጣት አይቻለንም፡፡ የስርዐት ለውጥ እንዳየነው ብቻውን ባዶ ነው፡፡ በዝች አገር ስር ነቀል ለውጥ እንዲመጣ የሚፈልግ ሁሉ ከላይ ከጠቀስኳቸው ሁለት ነገሮች በመሻገር በተሰማራበት ነፃና ጠንካራ ተቋማትን ለመፍጠር መነሳት ይኖርበታል!

No comments:

Post a Comment