Tuesday, 27 September 2016

የሰማያዊ ፓርቲ ፈተናዎች እና ተስፋዎች…


ሰማያዊ ፓርቲ በሰኔ ወር 2007 . ሁለተኛውን ጠቅላለ ጉባኤ ካደረገ በኋላ በፖለቲካው በኩል የጎላ እንቅስቃሴ ከማድርግ ይልቅ በውስጥ ችግሮች ተወጥሮ ሁኔታው አሁን ያለበት ደርሷል፡፡ ከዚህ በፊት በተለይ በፓርቲ ውስጥ ግልፅነትና ተጠያቂነትን አስመልክቶ እንዲሁም የተቃውሞ ጎራው አሁን ካለበት ተጠናክሮ እንዲወጣ ያስችለዋል ያልኩትን ሃሳብ እዚህ መድገም ስለማያስፈልግ ሊንኩን ኮሜንት መስጫው ላይ አስቀምጬ አልፋለሁ፡፡

-በቅርቡ ብሔራዊ ምክር ቤቱ ተሰብስቦ በፓርቲ መተዳደሪ ድንብ አንቀፅ 10/6 መሰረት የስራ አስፋፃሚውን የመተማመኛ ድምፅ ነፍጎታል፡፡ በዚህም መሰረት የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን ጠቅላላ ጉባኤ ለማካሄድ ሃላፊነቱን ተረክቦ ለዛሬ 14/01/2009 . ጠቅላላ ጉባኤ እንደሚካሄድ አስታውቆ ነበር፡፡ ሆኖም ከምርጫ ቦርድ በተላከ ደብዳቤ ማለትም ምርጫ ቦርድ ከጉባኤው በፊት ማጣራት ያለብኝ ጉዳይ ስላለ ጉባኤውን እንዲተላለፍ ሲል ጠይቋል፡፡ በዋነኝነት በዚህ ምክንያት ጉባኤው ሳይካሄድ ቀርቷል፡፡

የሆነው ሆኖ በፓርቲ ወስጥ ግልፅነትና ተጠያቂነት መኖሩ ሊደገፍና ሊበረታታ የሚገባው ተግባር ነው፡፡ የዛሬውን ብቻም ሳይሆን ነገ እንዲሆን የምንፈለገውን ለማየት የምንሻ ከሆነ ግልፅነትና ተጠያቂነት ለተቃውሞ ጎራው የህልውናም ጉዳይ ነው! ስለሆነም ሰማያዊ ፓርቲ እንደ አንድ አማርጭ ሃይል ሆኖ እንዲወጣ የምንፈልግ ከሆነ ለግለሰቦች ከማልቀስ በዘለለ ፖለቲካው እንዲዘምን ተነሳሽነት ማሳየት አለብን፡፡ አሁን እንደምናየው አሮጌውን የፍረጃ ፖለቲካ ማካሄድ ትንሽም ቢሆን የተካበውን ከማፍረስ ውጪ የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ ግለሰቦቹንም አይጠቅምም፣ ፓርቲውንና ትግሉንም አይጠቅምም፡፡

የተቃውሞ ጎራው የቅዱሳን ስብስብ አይደልም፡፡ አለመግባባቶች ሊኖሩ ይችላሉ፤ይህ ሲፈጠር የትኛውንም እርቀት ተሂዶ በፓርቲ አጥር ውስጥ ከመፍታት ይልቅ የተለመደውን እና ትላንት ለብዙ ግዜ ተሂዶበት ለውጥ ያላመጣውን መንገድ መምረጥ ምን የሚሉት ነው? እዚህ ላይ አንዳንዶቹ በውጭ ተቀምጠው በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ የሚያልፉትን በሰርጎገብነት ሲፈርጁ መመልከት አዲስ አይደልም፡፡ ቆይ እስኪ በፓርቲ ውስጥ ያሉ የትኞቹም ክፍሎች ደካሞች ቢሆኑ ለፓርቲው ምን ይጠቅማሉ? ጥርስ የሌለው ብሄራዊ ምክር ቤት፣ጥርስ የሌለው የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን ምን ይስራል? እነዚህ ክፍሎች የበላይ አመራሮችን የመጠየቅ አቅም በመፍጠራቸው ሊበረታቱ ሲገባ ዛሬም አንደትላንቱ በሰርጎገብነት ፈርጀን እንዴት ተቋማዊ ቁመና ያለው የለውጥ ሃይል መፍጠር እንችላለን?

ፖለቲካ የህዝብ እስከሆነ ድርስ በድብቅና በይሉኝታ የሚሰራ መሆን የለበትም፡፡ በጓደኝነት በሌላም በሌላም ምክንያት ጠበቃ ሆነው ሌላው ላይ ፍረጃ ሲያካሂዱ ይታያል፡፡ ይህ የተካበውን ከማፍረስ ውጪ አንዳችም የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ እንደውም የፍረጃ ትልቁ ችግር ወርቃማውንና ስልጡኑን በመከባበርና በእኩልነት ቁጭ ብሎ የመነጋገር እድልን መዝጋቱ ነው፡፡ ዛሬ እከሌ ሰርጎገብ ነው ብሎ ነገ በምን አይነት መንፈስ ነው ከእርሱ ጋር ቁጭ ብሎ መነጋገር የሚቻለው? ለማንኛውም ጠያቂ የለውጥ ሃይሎችን ጠያቂ በመሆናቸው ብቻ ተጠያቂ የማይሆኑበትን ሁኔታ ሊፈጥር አይገባም፡፡ መጠየቃቸው በምንም መንገድ እንደነውር መታየት የለበትም፡፡ ሊያስጨንቀን የሚገባው የግለሰቦቹ መጠየቅ ሳይሆን ከፍረጃና ከስሜት በመሻገር ነገ መፍጠር ለምንፈልገው ስርዐት መሰረቱን እያስቀመጥን ነው ወይስ አይደለም? የሚለው ነው፡፡

ፓርቲው ከፊቱ አሮጌው የፍረጃ ፖለቲካ፣የግለሰቦች አምልኮ እንዲሁም ከተጠያቂነት ጋር ተያይዞ ያሉት ነገሮች ጋሬጣ ሆነውበታል፡፡ ካለፈው ስህተት ጭምር በመማር ይህን መሻገር ካልተቻለ አድሮ ቃሪያ ከመሆን አይዘልም፡፡ ቁም ነገሩ ዛሬ ተሰብስበን ነገ መበታተናችን አይደልም፡፡ በመንገዳችን አስር ጊዜ ልንወድቅና ልንነሳ እንችላለን ነገር ግን ካለፈው ምን ይዘን መጣን? ከውድቀታችንስ ምን ተማርን? ነገስ የትኛውን መንገድ እንመርጣለን? ያሰብንበት እንድንደርስስ የትኛው መንገድ ይጠቅመናል? የሚለው መመለስ ያለበት ነው፡፡

በእርግጠኝነት የፓርቲው አባላት ከላይ ያለውን ከመለሱ ከፊታቸው ያለውን ፈተና የማለፍ ተስፋ አለ፡፡ እኔ በዚህ በኩል ተስፋ አልቆርጥም፤ ምክንያቱም ይህን ማድረግ የሚያስችል አቅም አለ! አሁን ላለው ችግር ዳኛው ምርጫ ቦርድ ሳይሆን የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ነው፡፡ ለምሳሌ አሁን ያለው ስራ አስፈፃሚ በቁጥር እንኳ የተሟላ አልነበረም፤በዚህ ላይ ከአመራር አሰጣጥ ጋር ተያይይዞ ከባህር ዳሩ ሰልፍ ጋር ተይይዞ የደረሰውን የምናውቀው ነው፡፡ አሁን ያለው አማራጭ እስካሁን ለነበሩ ችግሮች ላይ በጥልቀት በመወያየት መልስ ሰጥቶ ወደፊት ለመራመድ ለዚህም የፓርቲው ከፍተኛው አካል የሆነው ጠቅላላ ጉባኤ ትልቅ መድረክ ነው።

የአገዛዙ ነጠላ ዜማ ሶሪያንና ሊቢያን ትሆናላችሁ...

https://m.facebook.com/gracet.sewoch?ref_component=mbasic_home_header&ref_page=%2Fwap%2Fhome.php&refid=7


በአገሪቱ ውስጥ የተፈጠረውን ተቃውሞ ተከትሎ ስለ ሰላም በቁንፅል ትርጉም እየሰጡ ረጂም ዲስኩራቸውን እያሰሙ ነው፡፡ እዚህ ውስጥ ፊደል ከቆጠሩ አንስቶ ጌቶቹ የሰጡትን ሳያላምጥ እስከሚውጠው ካድሬ ድረስ ልፈፋቸው ተመሳሳይ ነው፡፡ ሌላው አስገራሚ ነገር ደግሞ የሰላም ተመራማሪ ነን የሚሉ የአገዛዙ የስጋ ዘመዶች ለሰላም የሚሰጡት ትርጉም ተመሳሳይ መሆኑ ነው፡፡ ለነሱ ሰላም ማለት ጦርነት የሌለበት ሁኔታ ነው፡፡ ለዚህ ቁንፅል ትንተናቸው ሲሉ የሚያቀርቡት ማስፈራሪያ አይነት ምሳሌ ሶሪያንና ሊቢያን አታዩም ወይ የሚል ነው፡፡

ለግልብ ትንተናቸው ማሳያነት ሶሪያንና ሊቢያን ያንሱ እንጂ የአላሳድንም ሆነ የጋዳፊን ፈላጭ ቆራጭነት እንዲሁም በአገሪቱ ውስጥ ለተነሱ የለውጥ እንቅስቃሴዎች በዋነኝነት ተገቢውን መልስ መስጠት ባለመቻላቸው በግልፅ ቋንቋ ስልጣን ወይም ሞት ባሉ የአገዛዝ ቆሞ ቀሮች ግትርነት የመጣ ግጭትና የእርስ በርስ ጦርነት እንደሆነ ደፍረው አይነግሩንም፡፡ ለምሳሌ የሁለቱን አገራት ሁኔታ በቅርብ የሚከታተሉ ተንታኞች በሶሪያም ሆነ በሊቢያ ከፀደዩ አብዮቱ በፊት የነበረው ሁኔታ ተመሳሳይ እንደሆነ ቢገልፁም ከአብዮቱ በኋላ የአገዛዙን ተፈጥሮአዊ ሁኔታ፣አለም አቀፍ ተፅእኖ፣በውስጥ ያለውን ሁኔታ፣ወታደራዊ እንቅስቃሴውን በማንሳት የሁለቱን አገሮች ሁኔታ አንድ አድርጎ ከመግለፅ ይልቅ ለያይተው ነው የሚያቀርቡት፡፡ የምሁርነት ካባ ያጠለቁ የኢህአዴግ የስጋ ዘመዶች ዋነኛ ጭንቀታቸው አገዛዙን በስልጣን ማቆየት በመሆኑ የሁለቱን አገራት ሁኔታ ለያይተው ሊያቀርቡ ቀርቶ የተረዱም አይመስልም።የወደፊቱን ሁኔታ የከፋ የሚያደርጉትም እንዲህ አይነቶቹ ናቸው፡፡

ሰላም የሚሉትም ጦርነት አለመኖሩንና ህዝቡ በፖሊስና በጦር ሃይል ተሰንጎ ተይዞ ጭጭ ብሎ በደሉንና ጥቃቱን ችሎ መገዛቱን ነው፡፡ ለማንኛውም ‹‹ጸጥ፣ለጥ ብሎ መገዛት ሰላም አይደልም፡፡›› በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች በቁንፅል የመልካም አስተዳደር ችግር ያውም የአገልግሎት አሰጣጥ አድርጎ በመተርጎም እንዲሁም በአገዛዙ ውስጥ ያሉ ሰዎች ስልጣን አላግባብ መጠቀማቸው ብቻ ነው የችግሩ ምንጭ ለዚህም እንታደሳለን ማለት ፌዝ ነው። ከዚህም ከፍ ሲል ሊብያንና ሶሪያን ትሆናላችሁ ብሎ ማስፈራራት እንደ ከዚህ ቀደሙ በማምታታት ጊዜን መግዛት ይቻል ይሆናል እንጂ የለውጥ ኃይሉን ማቆም ይቻላል ማለት ዘበት ነው፡፡

ሰሞኑን በተደጋጋሚ እንደተመለከትነው በቴሌቭዢን መስኮት እየቀረቡ እንታደሳለን የሚሉትን ነባር ነጠላ ዜማ አምኖ የሚቀበል የለም፡፡ ከአስር አመት በፊት በስመ ተሃድሶ የግለሰብ ፈላጭ ቆራጭነት ገኖ የወጣበት ነበር፡፡ አሁንም ተሃድሶ እናደርጋለን ሲሉን መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ሳይሆን ትናንሽ አሳዎችን በማጥመድ በሙስና ላይ ዘመትን በማለት እንዲሁም በተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች በንፁሃን ደም የጨቀዩ፣ በሙስና የተዘፈቁ አመራሮችን ከክልል አንስተው ወደ ፌደራል፣ከፌደራል አንስተው ወደ ክልል በማዘዋወር ጊዜን ለመግዛት ነው። ስልጣን ወይም ሞት ያለ የአገዛዝ ስርዐት ከዚህ ተሻግሮ መሄድ አይችልም።

የለውጥ ጠያቂዎች ደግሞ አገዛዙን ሁለትና ሶስት እጥፍ አልፈው የሄዱ ናቸው። እንዲሁ በአፋዊ እንታደሳለን በሚል ማሞኛ አልያም ሶሪያን ትሆናላችሁ እና መሰል ማስፈራሪያ አያቆመውም። መሰረታዊ ለውጥን ልክ እንደመሬት ፖሊሲው በመቃብራችን ላይ ነው ካሉ ለውጥ ተፈጥሯዊ ነውና በዛ መንገድ ይዳኛሉ። ለማንኛውም ፓርቲ ይመጣል፣ ፓርቲ ይሄዳል። አገርና ህዝብ ግን ይቀጥላሉ። ኢትዮጵያ ከኢህአዴግ ዘመን በፊትም ነበረች ከኢህአዴግ በሁዋላም ትኖራለች።
ጉዞ ከአገዛዝ ወደ ዲሞክራሲ