Thursday, 11 August 2016

በሰላም ትግል ጠላት የለም!

ይህን ፅሁፍ የምፅፈው በዋነኝነት በዚህ አገር በሰላም ትግል ለውጥ ለማምጣት በተግባር ደፋ ቀና እያሉ ላሉት ነው፡፡ አሁን ባለችው ኢትዮጵያ ሰላም ትግል እጅግ ከባድ እንደሆነ በተለይ ፖለቲካውን በቅርበት ለሚከታተል ቀርቶ ለአላፊ አግዳሚው ግልፅ ነው፡፡ በተለይ በስልጣን ላይ ያለው ስርዐት ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚወስዳቸው ሃላፊነት የጎደላቸው ድርጊቶች አገሪቷን ለበለጠ ችግርና አለመረጋጋት እየዳረጋት ይገኛል፡፡ በተለይ ቋንቋን መሰረት ያደረገው ፌደራላዊ አወቃቀር በእዝች አገር የጋራ መግባባት ከመፍጠር ይልቅ የችግሮች መፈልፈያ ሆኗል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ህዝብን የጎሪጥ እንዲተያይ አድርጎታል፡፡

 በተለይ ስርዐቱ የህዝብን መሰረታዊ ጥያቄዎች ከመመለስ ይልቅ የተለያየ ስም እየሰጠ የሄደባቸው መንገዶች በህዝብ ዘንድ ከቅሬታ አልፈው ቂም ቋጥረዋል፡፡ ለምሳሌ ያህል የህዝበ ሙስሊሙን የኃይማኖት ጥያቄ ይመሩ የነበሩ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ሽብርተኛ ተብለው ወህኒ ወርደዋል፤ጋዜጠኞች ሃሳባቸውን በነፃነት በመግለፃቸው ብቻ የሽብርተኝነት ታርጋ ተለጥፎባቸው በተመሳሳይ ወህኒ ወርደዋል፤ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና አመራሮችን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች የመብት ጥያቄዎችን ያነሱ ዜጎች እጣ ፈንታቸው ሞት፣እስር፣ድብደባ እንዲሁም ከአገር መሰደደ ሆኗል፡፡


 ስልጣን ላይ ያለው አካል በተለይ ከእሱ በተቃርኖ የቆሙ ኋይሎችን እንደ አጥፊ ኋይል በመቁጠር በአባላቶች ላይ፣ በአመራር ላይ እስርና እንግልት ከማድረስ በተጨማሪ ፓርቲ እስከ ማፍረስም ሄዷል፡፡ በግልፅ ቋንቋ ‹‹ተቃዋሚዎች እግር እስኪያወጡ እንጠብቃለን፤ ሲያወጡ እንቆጣለን›› ሲሉም ተደምጧል፡፡ በተቃውሞ ጎራውም ያሉት ለስርዐቱ በቂ ማስተማመኛ መስጠት አልቻሉም፡፡ መሃል መንገዱ እንዲርቅ የእነሱም ድርሻ አለበት፡፡ ይህ በተለይ ያለፈው ፖለቲካ ያሳረፈው ተፅእኖ ከመሆኑም በላይ የያኔ ተዋናዮች አሁንም ከላይ መኖራቸው መሃል መንገዱን እሩቅ አድርጎታል፡፡


 በተለይ ይህ መሃል መንገድ እንዲፈጠር የአንበሳውን ድርሻ ሊወስድ የሚገባው አገሪቷን እየመራ የሚገኘው መንግስት ቢሆንም እታች ወርዶ ተራ ጠብ ጫሪ ሆኗል፡፡ ሌላው ፖለቲካውን የከበበው ተዋናይም ከሩቅ ሆነ በለው፣ፍለጠው፣ቁረጠው በማለት ያሳደረው ተፅእኖ ቀላል አይደልም፡፡ አሁን እንደምናየው አገሪቷ በሁሉም በኩል ተወጥራ ትገኛለች፡፡ በዚህ ጊዜ ልብ ልንለው እና መርሳት የሌለብን በአገር እና መንግስት መካከል ያለውን ልዩነት ለደቂቃም ልንዘነጋ እንደማይገባ ነው፡፡


በተለይ በሰላም ትግል ፊት ለፊት ከስርዐቱ ጋር ተፋጣችሁ የምትገኙ ዜጎችም ሆነ የፖለቲካ ኃይሎች ሰርዐቱ ኃላፊነት የጎደለውን ተግባር ቢገፋም እናንተም እንደ ስርአቱ ተንሸራታችሁ ተዳፋቱን መውረድ የለባችሁም፡፡ እስከሚገባኝ አንድ ሰው ህይወቱን ጭምር በሚያሳጣ አስቀያሚ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ለመታገል ሲገባ ይህን የመሰለ ኃላፊነት ተሸክሞ ነው፡፡ ባለፈው ፖለቲካችን የደረሰው አስቀያሚ ነገር በዚህ ትውልድም እንዳይደገም የለውጥ ኃይሉ የሚቻለውን ሁሉ ሊያደርግ ይገባል፡፡


 ከላይ በርዕሴ ስነሳ በሰላም ትግል ጠላት የለም ብያለው፡፡ አዎ በሰላም ትግል ተፎካካሪ/ተቀናቃኝ እንጂ ጠላት የለም፡፡ ነገር ግን ስርዐቱ በሰላም ትግል የሚገጥሙትን ኃይሎች እንደ ጠላት ቆጥሮ ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት እየፈፀመ እንዳለ ግልፅ ነው፡፡ አሁን በበርካታ ችግሮች ተዘፍቃ ላለች አገር ስርዐቱን ተከትሎ መውረዱ ያለፈው አዘቅት ውስጥ ከመግባትና አገሪቷን ወደበለጠ አደጋ ከማስገባት ውጪ የተሻለ ለውጥ አያመጣም፡፡


 በዚህ ምክንያት የመሃል መንገዱ እንዲፈጠር፤ ስርአቱን በሰላም ትግል ፊት ለፊት የሚገጥሙ ሃይሎች ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው፡፡ እንደምናየው ፖለቲካውን የከበበው ከባቢ አየር በገዢ መደብና በተቀረው ህዝብ መካከል ያለውን ትለቅ ድንበር መለየት እንኳን አቅቶታል፡፡ ስርዐቱ አሁንም በርካታ አባላትና ደጋፊዎች ያሉት፣ አሁንም በፌደራልም በክልልም ያሉ ሁነኛ ኃይሎችን እንደሚዘውር ሁሉ ተረስቷል፡፡ ይህ ሁሉ በሆነበት ሁኔታ ቁረጠው፣ፍለጠው አካሄድ የትም አያደርስም፡፡


 ስለዚህ የሚደረገው ትግል በስልጣን ላይ ላሉ ሰዎች፣ለአባላቶቹ እንዲሁም ለደጋፊዎቹም ጭምር ዋስትና የሚሰጥ መሆን አለበት፡፡ ይውደም ይጥፋ እያሉ ሰላም ትግል የለም፡፡ ይህም መኃል መንገዱን ከመፍጠር ይልቅ አገሪትዋን ወደ ማትወጣበት አዘቅት የሚከት ነው፡፡ ስለሆነም ከስርዐቱ እንድ እርምጃ ተሻግሮ ማሰብ ብቻም ሳይሆን መተግበር ግድ ይላል፡፡ ምክንያቱም በባሌም በቦሌም ኢህአዴግን ከዙፋኑ እንዲወርድና እንዲወርድ መመኘት ብቻውን በአገራችን እንዲሆን ለምንናፍቀው ስርዐት ምንም ፋይዳ አያመጣም፡፡

No comments:

Post a Comment