Tuesday, 23 August 2016

‹‹በሰለጠነ አገር በምቾትና በድሎት እየኖሩ… ሰላማችንን ለማደፍረስ…››

በኮሚዩንኬሽን ጉዳዮች የተሰራጨ እንደሆነ ያደመጥኩት እራሷን የወረዳ ሰባት ነዋሪ እንደሆነች የገለፀች እንስትን ንግግር ሰማሁት ከአንዴም ሁለቴ፤ እንስቷ ግን በፓርቲ ፍቅር አቅሏን ስታ አዲስ ነገር ልትነግረን ቀርቶ ‹‹ለምን እዚህ መጥተው በጫካ አይፋለሙም›› ሁሉ ስትል ተደምጣለች፡፡ ስርዐቱ አሁንም የህዝብን ጥቄዎች ከማድመጥ ይልቅ የራሱን ሰዎች እንዲናገሩ እያደረገ የራሱን ድምፅ መልሶ እየሰማ ይገኛል፡፡ 


እዚህ ጋር ሁለት ነገሮችን ማየት ያስፈልጋል፡፡ አንደኛው ‹‹በሰለጠነ አገር በምቾትና በድሎት እየኖሩ ልጆቻችንን እሳት ውስጥ ለመማገድ›› የሚለው ሲሆን ሁለተኛው ‹‹ሰላማችንን ለማደፍረስ›› የሚል ነው፡፡ ይህ ተደጋግሞ እየተስተጋባ ያለ ነገር ነው፡፡ ከመጀመሪው ስጀምር በማንም ቀስቃሽነት አስተዋዋቂነት ሰልፍ ቢወጣ፤ ሰልፍ ወጪው አላማውን አምኖበትና ተቀብሎት እስከወጣ ድረስ ባለቤቱ ሰልፉን የሚያካሂደው ነው፡፡ ይህ ማለት ግን የሰልፉን እቅድ በውጭ የሚገኙ ሰዎች ማውጣት አለባቸው ማለት አይደልም፡፡ ይህን እንደየ አውዱ የመወሰን ስልጣን ያለው በቀጥታ በሰልፉ የሚሳተፈው ብቻ ነው፡፡ 
 
-
ባደባባይ ጭምር ባለማፈር የእነዚህን ዜጎች የመቀስቀስና የማስተዋወቅ ሚና የሚወጡትን የተለያየ ስም እየሰጡ እርግማን የሚያወርዱባቸው ዋነኛውን የመንግስትን ህገ አራዊት ተግባር ለመሸፈን ይመስላል፡፡ ዜጎች ሰላማዊ ሰልፍ ሳያስፈቅዱ (ማስፈቀድ የሚል ነገር ካለም ማለቴ ነው) በመውጣታቸው ብቻ ሰላምን በማስከበር ስም የዜጎችን ሞት ግን በምንም መንገድ ትክክል አያደርገውም፡፡ የስርዐቱ ሎሌዎች አለቆቻቸው የሚሉትን እያስተጋቡ ያሉትን ጨምሮ አነብናቢ ሚድያዎች እንዲሁም ይህን ባለማወቅ የሚደግሙ ሰዎች ስርዐቱ በንፁሃን ላይ የሚወስደውን ሞት፣ እንግልትና እስር ትክክል ነው እያሉ ነው፡፡ይህ የቱንም አይነት ምክንያት ቢቀርብ ትክክል አያደርገውም፡፡ ለገዢዎቹም ጊዜ ከመግዛት በቀር የሚያመጣው ነገር የለም፡፡ ለአገራችን ግን መጥፎ ባህል በመትከል ኢትዮጵያን የአንባገነኖች ቤተ ሙከራ የሚያደርግ ነው፡፡



ወደ ሁለተኛው ስመጣ ሰላም የሚለው ነው፡፡ ይህን ፅሁፍ እየፃፍኩ በቴሌቭዢን መስኮት ቀርበው ግለሰቦች አስተያየት እየሰጡ ነበር፡፡ ‹‹ህዝቡ ሰላም ወዳድ መሆኑን አሳይቷል፡፡›› ከሚሉት እንቶ ፈንቶዎች ጀምሮ የተለመደው ሰላማችንን ለማደፍረስ የሚለው በተለያየ መንገድ ተደጋግሞ የሚስተጋባ ነው፡፡ ለነዚህ ሰዎችና ላዘዟቸው ገዢዎች ጦርነት ባለመኖሩ ብቻ ሰላም አለ ማለት ነው፡፡ ኃይለኞቹ ገዢዎች ደካሞችን አስገብረው፣በጉልበታቸው የሰውን ልጅ መንፈስ ገድለው፣አእምሮው ታዛዥና ተገዢ ብቻ እንዲሆን አድርገው በድኑን አንደአሻንጉሊት በሚጫወቱበት ሁኔታ ሰላም አለ ይላሉ፡፡ 


‹‹አንድ ህዝብ በፖሊስና በጦር ሃይል ተሰንጎ ተይዞ ጭጭ ብሎ በደሉንና ጥቃቱን ቢችል ሰላም ነው ማለት አይደለም፡፡ ኃይለኛ ደካማውን ሲያጠቃ ሰላም የለም፤ብዙዎች ጥቂቶችን ሲያጠቁ ሰላም የለም፤ጥቂቶች ተደራጅተውና ታጥቀው ብዙዎችን ሲያጠቁ ሰላም የለም፡፡ ጸጥ፣ለጥ ብሎ መገዛት ሰላም አይደልም፡፡›› ጸጥ፣ ለጥ ብሎ መገዛት ሰላም የሚመስላቸውና ይህን ድንቁርናቸውን ለሌላው የሚግቱ ሰዎች ነገን እያበላሹ እንደሆነ አልገባቸውም፡፡

No comments:

Post a Comment