Wednesday, 6 May 2015

የሙስሊሙ መንገድ!



ከአንድ አመት በፊትየሙስሊሙ ተቃውሞ እና ቀጣዩ የሰላማዊ ትግል እጣ ፈንታየሚል አንድ ፅሁፍ ፅፌ ነበር፡፡ በወቅቱ ይህን የሙስሊሙ ሰላማዊ ጥያቄ ጥላሸት ለመቀባት በርካታ ሴራዎች ሲሴሩ እንደነበር በመመልከት ስጋቴንም ጭምር በመግለፅ ትብብር ማድረግ አንዳለብን ገልጬ ነበር፡፡ በእስካሁኑ የድምፃችን ይሰማ የሙስሊሙ ህብረተሰብ ሰላማዊ ጥያቄዎች በርካታ የስርዐቱን ሴራዎች እያከሸፉ እዚህ ደርሰዋል፡፡ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ጥያቄዎቹ እስኪመለሱ ድረስ እያሳየ ያለው ቆራጥነት ያብብ ይለምልም የሚያስብል ነው፡፡


ይኸው የሙስሊሙ ህብረተሰብ ያነሷቸው ተቃውሞዎች ማለትም የአወሊያ በቦርድ ይተዳደር፣ መንግስት ከሐይማኖቱ እጁን በማንሳት ሙስሊሙ ህብረተሰብ መሪዎቹን መምረጥ እንዳለበት፣ እንዲሁም ሙስሊሙ ህብረተሰብ ላይ በግዴታ የሚጫነው የአህባሽ ስተምህሮ እንዲቆም የሚል ነበር የሙስሊሙ ጥያቄ፡፡ ለነዚህ ጥያቄዎች መሳካት ከመንግስት ጋር እንዲደራደሩ የወከሏቸው የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት በስርዐቱ መታሰራቸውን ተከትሎ ጥያቄዎቹ ላይ የሙስሊሙ ህብረተሰብን የወከሉ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ይፈቱ የሚል ተጨመረበት፡፡


ከፋፋዩና አምባገነኑ ስርዐት ህዝበ ሙስሊሙ የጠየቋቸውን ጥያቄዎች ወደ ጎን በመግፋት ንፁሃንን በማሰር፣ ሰላማዊውን የሙስሊሙ ህብረተሰብ ጥያቄዎች ጥላሸት ለመቀባት እንደ ‹‹ጀሃዳዊ ሃረካት›› አይነት ልብወለድ ዶክመንተሪዎችን ጭምር በመስራት ብዙ ለፍቷል፡፡ ይህን ሁሉ በመቋቋም የድምፃችን ይሰማ ተቃውሞ ሶስት አመታትን ደፈነ፡፡ ይህ ሰላማዊ ተቃውሞ በቅርቡ አንድ እርከን ከፍ በማለት ተቃውሞው ጥብብር ወደ መንፈግ ተዘዋወረ፡፡ ምናልባትም አብዛኛው ተቃውሞው ላለፉት ሶስት አመታት በመስጂድ ከመካሄዱ አንፃር ይህን ሰላማዊ የሙስሊሙ ህብረተሰብ ተቃውሞ ከእምነቱ ውጪ ያሉት ዜጎች ለመካፈል አይችሉ ይሆናል፡፡


አሁን ላይ ግን ይህ ሰላማዊ ጥያቄ ትብብርን ወደ መንፈግ በመዘዋወሩ ማንኛውም ዜጋ ይህን ሰላማዊ ጥያቄ በመደገፍ ከሙስሊሙ ህብረተሰብ ጎን መቆም ይቻለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የተካሄደውን ማለትም ስልክን የማጥፋት እንዲሁም አሁን በመካሄድ ላይ ያለውን ሳንቲሞችን ሰብስቦ በመያዝ እየተካሄደ ያለ ነው፡፡ በዚህ መንገድ ለስርዐቱ ትብብርን መንፈግ ያን ያህል የጎላ አደጋ የማያስከትል በመሆኑ በቀላሉ አጋርነታችንን ማሳየት ይኖርብናል፡፡ መክንያቱም በየደረጃው ያለ ዜጋ መሳተፍ በሚችለው አቅም ያህል ማድረግ የሚያስችለው በመሆኑ ድር ቢያብርእንዲሉ አጋርነታችንን በማሳየት ስርዐቱ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ያነሷቸውን ጥያቄዎች እንዲመልስ ማስገደድ ይኖርብናል፡፡


በታሪክም እንዳየነው ከፋፋይና አምባገነን መሪዎች ፈቅደው አልያም ወደው የሰጡት መብት የለም፡፡ ተገደው እንጂ! ሙስሊሙ ህብረተሰብም ለሶስት አመታት ያካሄደው ተቃውሞ በአንድ እርከን ከፍ ያለው ይህን ተከትሎ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም እንዳልኩት ይህ በሰላማዊነቱ ወደር የሌለው እና እስካሁን ከተካሄዱት የመብት ጥያቄዎች በተለየ መንገድ ሳይቋረጥ ለሶስት አመታት የዘለቀው የሙስሊሙ ህብረተሰብ ጥያቄ መልስ ሳያገኝ ቢቀር ወደፊት በዝች አገር የሚካሄዱ ሰላማዊ ትግሎችን አስቸጋሪ ያደርጋቸዋል፡፡ ለዚህ ነው የሙስሊሙ ተቃውሞ እና ቀጣዩ የሰላማዊ ትግል እጣ ፈንታ ማለቴ! በተለይ ይህ ጥያቄ ከግብ የሚደርስ ከሆነ በዝች አገር ለሚነሱ የመብት ጥያቄዎች መቆጥቆጥና ማበብ የሚኖረው ድርሻ የጎላ ነው፡፡ እናም ትብብር ልናደርግ ይገባል ፡፡



ላለፉት ሶስት አመታት ሲካሄድና አሁንም በመካሄድ ላይ ያለውን ሰላማዊ የሆነውን የሙስሊሙ ህብረተሰብ ጥያቄ፤ ከፋፋይ እና አምባገነን ገዢዎች እንዲሁም ከሃይማኖታቸው አጥር ተሻግረው ማሰብ በማይችሉ የሃይማኖት ሰዎች በሚሰጡት የተሳሳተ ትርጉም እንደወረደ ተቀብለሽ/ ለዚህ በሰላማዊነቱ ወደር ላልተገኘለት ሰላማዊ ጥያቄ ጀርባህን የምትሰጥ/ ነገ የተቋምነት ጥያቄ ስታነሱ አሁን በሙስሊሙ ላይ የሚደርሰው ህገወጥ ድርጊት ነው የሚከተላችሁ፡፡ ይህ ከመሆኑ በፊት የገዢዎችን ከፋፍለህ ግዛ እስትራቴጂ እግረ መንገዳችንን እያከሸፍን እንዲሁም ወደፊት ለሚነሱ ሰላማዊና ህጋዊ ጥያቄዎች በዚች አገር አንዲያብቡ በር ለመክፈት ጭምር ከመንገድ ያለውን የሙስሊሙ ድምፃችን ይሰማ ጥያቄ ጎን በመቆም አገርነታችንን ልናሳይ ይገባል፡፡

No comments:

Post a Comment