Wednesday, 6 May 2015

ትውልዱ ወደ ራሱ አጀንዳ ሊመለስ ይገባል!


ስለዚህ ትውልድ ብዙ ብዙ ተብሏል፡፡ አሁን ላይ ብዙ ስለተባለለት ነገር የመፃፍ ፍላጎቱ የለኝም፡፡ በእርግጥም በዚህ ትውልድ ላይ የሚነሱ ትችቶች በሙሉ ምንም መሰረት የሌላቸው ናቸው ለማለት አልደፍርም፡፡ ምናልባት ትችቶቹ ይበልጥ ተጋነው ገንቢ ባልሆነ መንገድና ጥሩ ባልሆኑ ቃላት መገለፃቸው ስህተት ሊሆን ይችላል፡፡ ትውልዱ ከገባበት ቀውስ ለመውጣት ብቻም ሳይሆን ስለ ወደፊቱ እጣ ፈንታው ለመወሰን ቅድሚያ ወደ ውስጥ በጥልቀት በመመልከት ስህተቶቹን በማረም ወደፊት ሊገሰግስ ይገባል ባይ ነኝ፡፡


እኔና የእድሜ እኩዮቼ አሁን ለገባንበት ቀውስ ያበቃን ገና ሳይጠሩን ወዴት እንሂድ? በየትስ በኩል እንለፍ ማለታችን አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ አሁን ያለንበትን ጨምሮ ነገም በሌሎች አጀንዳ ላለመፍሰሳችን ምንም ዋስትና የለውም፡፡ የዚህ ፅሁፍ አላማ ለዚህ ገድብ ልናበጅለት ይገባል ነው፡፡ በአውራፓ እግር ኳስ እንዝናና ይሆናል፡፡ ይህን ያህል አቅላችንን ስተን ግን እስከሞት ለመድረስ የሚያበቃ ሚጢጢ ምክንያት ሊሆነን አይችልም፡፡ አሁን መሬት ላይ ባለው ሁኔታ በርካታ የሬዲዮ ፕሮግራሞች በእዝች ዘርፈ ብዙ ችግር ባለባት አገር የአውሮፓ እግር ኳስ ተዘርቶ የሚታጨድ ይመስል የሚነዙት ወሬ ብታምኑም ባታምኑም አገራችን በእግር ኳሱ ስላደገች ሳይሆን እኔንና የእድሜ እኩዮቼን ትኩረት ለማስቀየስ እንደሆነ እሙን ነው፡፡


ላለፉት አስር አመታት እንደታዘብነው በአቅራቢያችን እንደ አሸን እየፈሉ ያሉትን የጫትና የሺሻ አንዲሁም ዳንኪራ ቤቶችን እሩብ ያህል እንኳ ቤተ መፅሐፍቶች ሲከፈቱ አላየንም፡፡ ከላይ እንዳልኩት ሬዲዮኖቻችንና ቴሌቭዢኖቻችን በዝች አገር ከእግር ኳስና በተለምዶ ፍቅር ከሚባለውና ከአልጋ ላይ እሩጫ መሻገር ከማይችለው ግንኙነት ሌላ አጀንዳ የሌለ እስኪመስል ድረስ የተሄደበት መንገድ ትውልዱን ከራሱ አጀንዳ ለማራቅ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ በዚህም ሂደት ከራሳቸው አልፈው ማሰብ ያልቻሉ የቀን ጅቦች ኪሳቸውን ያለቅጥ ሲያደልቡበት ከፋፋይና አምባገነን መሪዎች ዛሬም ትውልዱን የሚገልና በራሱ አገር ባይተዋር የሚያደርግ ፖሊሲያቸውን ይዘው ዛሬም ከላይ እንዲቀመጡ ምክንያት ሆኗል፡፡


እንደምናየው ትውልዱ በተለያየ ካታጎሪ እንዲፈስ ከተዘጋጁለት ጅረቶች ሌላው ላለፉት ሀያ ሶስት አመታት ያለዜጎች ይሁንታ ዜጎችን ከፋፍሎ ለመግዛት እንዲመች ሲባል የተዘጋጀው ቋንቋን መሰረት ያደረገ ፌደራሊም አንዱ ነው፡፡ በእርግጥ ይህ የገዢዎች ሴራ በተለይ በወጣቱ ትውልድ ላይ ሙሉ በሙሉ ውጤታማ አንዳልሆነ መናገር ይቻላል፡፡ ይህ ማለት ግን ከዚህ የገዢዎች ወጥመድ ነፃ ነን ማለት አይደለም፡፡ እርስ በራሳችን በጥርጣሬ እንድንተያይ የጋራ አጀንዳ እንዳንቀርፅ ለዚህም ተግባራዊነት ከልብ እንዳንሰራ አድርጎናል፡፡ ሌላው ቀርቶ ከሚያግባቡን ብዙ ጉዳዮች ይልቅ የሚያለያዩን ጥቂት ጉዳዮች ላይ እያወቅንም ይሁን ሳናውቅ ትኩረት በማድረግ ለሌሎች አጀንዳ እጅ ሰጥተናል፡፡


ከላይ ባነሳነው ምክንያት ተነስተው ትውልዱን ባለፈ ታሪክ ሂሳብ እንዲያወራርድ የሚፈልጉ ሰዎችም አሉ፡፡ ይህም በተጨባጭ ፈጠው ከሚታዩ የትወልዱ አጀንዳዎች ሊሰለፍ የሚችል አይደለም፡፡ ይህ አላማ ያላቸው ሰዎች ለዚህ አላማ መሳካት ይረዳቸው ዘንድ የሄዱበት መንገድ አስተዛዛቢና አሳዛኝ ነው፡፡ ይህ ትውልድ እነሱ እንደሚፈልጉት ሂሳብ ቢያወራርድ ለዚህ ትውልድ ጠብ የሚልለት ነገር ምንድን ነው? ለሌሎች አላማ መጠቀሚያ ሆኖ ምጡን ከማርዘም በቀር፡፡ እርግጥ ነው ልዩነቶች ይኖራሉ ነገር ግን በዚህ በግሎባላዬዜሽን ዘመን አለም የአንድ መንደር ያህል በጠበበችበት ሁኔታ በሌሎች ሴራ ተታለን አንዳችን አንዳችንን በጠላትነት እየተመለከትን እዛችው ቅርጫታችን ውስጥ ሆነን እስከመቼ እንዘልቃለን?



አሳዛኙና ከርታታው የእኔ ትውልድ በአገሩ ጉዳይ እንኳ የሌላ ዜጋ ያህል ሆኖ በመኖር ይህም ሲከፋበት ስደትን እንደ አማራጭ በመውሰድ እድለኛ የሆኑ በርካታ ኪሎሜትሮችን አቋርጠው እንዳሰቡት ትንሽ ተንፈስ ሲሉ አብዛኛዎቹ አስቸጋሪውን የድንበር ማቋረጥ መቋቋም አቅቷቸው በየበረሓው ወድቀውና በየባህሩ ሰጥመው ቀርተዋል፡፡ አሁንም እንደምንሰማው በየቦታው ተበትነው ላሉት ዜጎች ህመማቸውን የሚታመምላቸው ጥቃት እንዳይደርስባቸው ከጎናቸው የሚቆም መንግስት አጥተው ይኸው መድረሻ እንዳጡ ናቸው፡፡


ይህ ሁሉ ሆኖ ግን አሁንም በየሬዲዮውና በየቴሌቪዢኑ ‹‹የነገ አገር ተረካቢ የሆነው ትውልድ›› የምትል ለቧልት የቀረበች ንግግር ደጋግመን እንሰማለን፡፡ ይህ የሚያሳየው ባንድ በኩል ፌዟ እንዳለች ሁሉ ገዢዎቻችን ለኛ ያላቸውን ንቀትም ጭምር እየገለፁ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ በተጨባጭ በሁሉም ሊባል በሚችሉ ቦታዎች አሁንም ወጣቱ ትውልድ ገሸሽ እንዲደረግ ሆኗል፡፡ አገር የሚረከበውስ መቼ ነው? ትላንት ዛሬ እያሉን ነበር፡፡ ዛሬ ላይስ ነገ እያሉን አይደለምን? ይህ ምን ያስታውሰናል መሰላችሁ አንድ ባለ ሱቅ ‹‹ዱቤ ከፈለጉ ነገ ይምጡ›› ብሎ የለጠፋትን መልዕክት፡፡ ምናልባትም ይህ ትውልድ አገር ተረካቢ እየተባለ ወደ እርጅና አለም የገባ የመጀመሪያው እንዳይሆን ያሰጋል፡፡

 
እንደምናየው ሶሻል ሚዲያውን እንኳ ተደራሽነቱን እንደ በጎ አጋጣሚ በመጠቀም ብዙ መስራት ስንችል እንዲሁ በሆነውና ባልሆነው ቃላት በመወራወር ጊዜያችንን እያጠፋን እንገኛለን፡፡ ልዩነቶችን በመዝራት የራሳቸውን አጀንዳ ለማራመድ ለሚፈልጉ ሰዎች ምቹ ሆነን ተገኝተናል፡፡ በቅርቡ እንኳ መገንጠል የሚለውን ነገር ገና የሰማን ይመስል ብዙ ጊዜያችንን ስናጠፋ ተስተውለናል፡፡ ሰሞኑን ስለ ቦብ ማርሌ ሀውልት መቆም እና ስለ ኤድናሞል ስላወጣው የአለባበስ ሁኔታ አስመልክቶ የሚደረጉ ክርክሮች አስቂኝ ናቸው፡፡ ከዘጠና ሚሊዮን ህዝብ በላይ ባለበት አገር አንድ ከመቶ ህዝብ እንኳ በማይዝናናበት ሚጢጢ የመዝናኛ ማእከል እንደትልቅ አጀንዳ ጉዳያችን ማድረጋችን አሳፋሪ ነው፡፡ ነገስ በማን አጀንዳ እንከራከር ይሆን? ይህ እና ከላይ የጠቀስኳቸው በሙሉ ከራሳችን አጀንዳ ምን ይህል እንደራቅን ትልቅ ማሳያ ናቸው፡፡
ምን እናድርግ


‹‹ቀደምትን በጠላትነት ከመፈረጅና ከመርገም በቀር ያለፈውን አውቆ፣የአሁኑን ተረድቶ መጪውን ለማለም የማይችል ብኩን ዜጋ ነው ለማለት ያስደፍራል›› እንዲሉ ምሁሩ / ገብሩ ታረቀ ትውልዱ ባለፉት ጊዜያት በሆኑ ነገሮች ጊዜውን እንዲሁም ቢሰራበት ውጤታማ የሚሆንበረትን ጉልበት ቁጭ አርጎ ትላንት ስለሆነው ነገር ያለፉትን እህትና ወንድሞቹን በጠላትንነት በመፈረጅና በመርገም በተጨባጭ ምንም ጠብ ያረገለት ነገር የለም፡፡ እንደ ምሁሩ ምክር የትውልዱ ጉዳይ ያለፈውን አውቆ የአሁኑን ተረድቶ መጪውን ማለም ይገባዋል፡፡


እርግጥ ነው በታሪክ በኩል መልካምም ሆነ ስህተት ነገሮች ተሰርተው ይሆናል፡፡ አሁን ያለው ወጣት በዚህ ጊዜ እንዲህ ተደረገ እንዲህ ሆነ በሚል አሉታዊ ነገር ብቻ ተለጥፎ ወደፊት እንዳይራመድ የሚደረገው የገዢው ፓርቲና የአንዳንድ ተቃዋሚ ተብዬዎች ሴራን ይህ ትውልድ ሊያከሽፈው ይገባል፡፡ ወጣቱ ሊያደርግ የሚችለው በታሪካችን ውስጥ ያለፉትን በጎ ነገሮች በመቀበል በሌላው አንፃር ደግሞ ጥሩ የማይባሉትን እያስተካከለ ወደፊት መሄድ እንጂ ገዢዎቻችን እንደሚፈልጉት ትላንት ላይ ተለጥፈን የጎሪጥ እየተያየን የነገ ብሩህ ጊዜያችንን ማበላሸት ማቆም ይኖርብናል፡፡


 
ሌላውና ዋነኛው በየትኛውም መንገድ ቢሆን ገዢዎች ካሰመሩት የከፋፍለህ ግዛ መስመር መውጣት ግድ ይላል፡፡ ዛሬ በወገኖቻችን ላይ የሚደርሰውን አይተን ቸል የምንለው አይደለም፡፡ ምክንያቱም ገዢዎቻችን በሳይንሳዊ ቀመር ሳይሆን የሚመሩን ባረጀው እና ባፈጀው ከፋፍለህ ግዛ ነው፡፡ እናም በዚህ ዝምታችን ከቀጠልን የነገ ተረኞች መሆናችንን መርሳት የለብንም፡፡ እናም በፍጥነት ለጋራ ጉዳያችን በጋራ መቆም ይኖርብናል፡፡ አስከመቼ እራሳችንን ይህንም ያንንም መሞከሪያ እያደረግን እንዘልቃለን? እስከመቼስ ሌሎች በቀደዱልን እየፈሰስን አንዳክራለን? ከዚህ በመሻገር የራሳችንን መንገድ መከተል ይኖርብናል፡፡


ከላይ ለማለት አንደሞከርኩት የትወልዱ ዋነኛ ችግር ከአጀንዳው ውጪ አለቅጥ መፍሰሱ ነው፡፡ ይህን ተረድተን በምናከናውናቸው እያንዳንዷ ጉዳይ በራሳችን አጀንዳ ላይ መሆናችንን ማረጋገጥ መቻል ኖርብናል፡፡ አሁን ሌሎች በቀደዱልን ፈሰን እያደረግን ያለነው ነገር በተጨባጭ ህይወታችን ላይ ምንድን ነው እያረገ ያለው? ነገስ ወዴት ነው የሚወስደን? እንደ ትውልድስ የነገ እጣ ፈንታችን ምንድን ነው? እስከመቼስ ድረስ ነው በተስፋቢስነት ወስጥ ሆነን የምንዘልቀው? እንደዜጋስ ለአገራችን ማድረግ የሚገባን ምንድን ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች ከስሜት በዘለለ መመልከትና መልስ መስጠት ይኖርብናል፡፡
ጥሩውን ተመኘሁ!

No comments:

Post a Comment