Wednesday, 6 May 2015

ISIS፤እስልምና፣ሽብርተኝነት…?



መቼም ሰሞኑን እየደረሱ ያሉ አረመኔያዊ ድርጊቶች ሁላችንንም አንገት ያስደፋ ነው፡፡ አዎ ይህ ሰው ለሆነ ሁሉ ህመም ነው፡፡ የደረሰው ድርጊት በየትኛውም ላይ እንዲደርስ የማንሻው እንስሳዊ ድርጊት ነው፡፡ በእርግጥም እንደ አገር የየመኑን ሳንረሳ የደቡብ አፍሪካው ከሱም ሳናገግም በሊቢያ የተፈፀመው እንስሳዊ ድርጊት ሃዘናችንን አበርትቶታል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ተሁኖ መፃፍ ቢያሰቸግርም ለጥንቃቄ ያህል ሁለት ነጥቦችን አነሳለሁ፡፡


አንደኛው እራሱን ISIS(Islamic state Iraq and syria) እያለ የሚጠራው የእንስሳቶች ስብስብ ለይስሙላ የሐይማኖት አጀንዳ አንግቦ ከዚህ ቀደም እንዳየነው በተለያየ ቦታ አራዊታዊ ተግባር ሲፈፅም ተስተውሏል፡፡ ይህም በየትኛውም ሁኔታ ተቀባይነ የሌለው ከመሆኑም አንፃር የየትኛውንም ሃይማኖት የሚወክል አይደለም፡፡ አንድ አካል የዚህ ሃይማኖት ተከታይ ነኝ ብሎ የሚፈፅመው እንስሳዊ ተግባር ሚሊዮኖች የሚከተሉትን ሃይማኖት ሊወክል አይችልም፡፡ እንደዚህ አይነት ውክልናም በየትም ቦታ የለም፡፡ ስለሆነም ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳውን መሬት ላይ ፈጦ ከሚታየው እውነት ያፈነገጠ ነገር ልንታለል አይገባም፡፡ እስኳሁን እንዳየነው ይህን የእንስሳዎች ስብስብ ድርጊት አለም እያወገዘው ነው ያለው፡፡ እስከሚገባኝ ይህ የአራዊቶች ስብስብ እስልምናን ስለማወቁ እጠራጠራለሁ፡፡ ስለሆነም ይህን የአራዊት ስብስብ ከእስልምና ጋር አያይዞ ማየት ፍፁም ስህተት ነው፡፡ አይ ኤስ እስልምናን የሚወክልበት ነገር የለም፡፡ ምናልባትም የሙስሊም ሃይማኖት ላይ ጥላሸት ለመቀባት የተነሳ ስብስብ ሳይሆን አይቀርም፡፡

 
ሁለተኛው የእኛው ከፋፋይና አምባገነን ስርዐት በተለይ ከሽብርተኝነት ጋር እያያዘ ንፁሃንን እያሰረ እያሰቃየ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ አሁን በስርዐቱ ሚዲያዎች ከዚህ ቀደም አንደሚሉት በሊቢያ የደረሰውን ድርጊት አስታከው ቀድሞ ሲነዛው የነበረውን ፕሮፓጋንዳ እያስተጋቡት ነው፡፡ ዛሬም በድፍረትየጀመርነውን የፀረ ሽብር ዘመቻ እንገፋበታለንእያሉ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም አንዳየነው የሃይማኖት ነፃነት የጠቁትን የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን እንዲሁም ጋዜጠኞችን ጦማሪያንን የፖለቲካ መሪዎችን አስሮ እያሰቃየ ይገኛል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ነገም ንፁሃንን በገፍ ወደ ወህኒ እንዳያወርድ ስጋት አለ፡፡ የቱንም ያህል የለመዱትን ፕሮፓጋንዳ ቢነዙ ዛሬም በስመ ሽብር የታሰሩት ንፁህን ዜጎች እንደሆኑ እንመሰክራለን፡፡ ሽብርን የሚጠየፉ ዜጎች እንጂ ሽብርተኞች አይደሉም፡፡ ምንም እንኳን ሽብርተኝነትን ብንቃወምም በአገራችን በንፁሃን ላይ የሚለጠፈውን የሽብርተኝነት ታርጋ አጥበቀን እንቃወማለን፡፡ ከአለም አቀፍ ሁኔታዎች በተለየ ሁኔታ በአገራችን ሽብርተኝነትን አስመልክቶ የተሰጠውን ትርጉም አጥብቀን እናወግዛለን፡፡ ስለሆነም ከዚህ አንፃር የስርዐቱን ባዶ ፕሮፓጋንዳ ማክሸፍ አለብን፡፡

 
የሞቱትን ነፍሳቸውን ይማርልን ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን ይስጥልን!

No comments:

Post a Comment