ይህን ፅሁፍ የምፅፈው የተቃውሞ ጎራው ካለፉት ስህተቶች በመማር ነገን ተጠናክሮ እንዲወጣ ካለኝ ፍላጎት እንጂ አንዱን ለማሳነስ ሌላውን ከፍ ለማድረግ ከመነጨ አይደለም፡፡ ከዚህ በፊት እንዳልኩት የፍረጃ ፖለቲካ አይጠቅመንም፡፡ በችግሮቻችን ላይ ግን በግልፅ መነጋገር ይገባናል ባይ ነኝ፡፡ እስካሁን ባለው የተቃውሞ ጎራው ስብስብ ግለሰቦች በሚፈጥሩት ያልተገራ ድርጊት ትግሉ የሁዋሊት ሲጓዝ ተመልክተናል፡፡ በዚህም ቀላል የማይባል ሰው ተስፋ ቆጧል፡፡
በቅርቡ በአንድነት እና በመኢአድ ውስጥ የሆነው ብናይ እንኳን ትግሉ ነው ወይስ የግለሰቦች ፍላጎት ነው መቅደም ያለበት ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል፡፡ የአንድነት ሊቀመንበር ወ/ሪት ብርትኳን ለእስር መዳረጓን ተከትሎ ፓርቲውን መምራት የጀመሩት ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው በ2004 ስልጣናቸውን ለቀድሞ ፕሬዚደንት ዶ/ር ነጋሶ ማስረከባቸው ይታወሳል፡፡ቃል በቃልም ባይሆን በወቅቱ ያቀረቡት ምክንያት ፖለቲካ ከውስጤ ወጥቷል የሚል ነበር፡፡ ፓርቲውን ዶ/ር ነጋሶ በሚመሩበት ጊዜ ኢንጅነሩ ያደረጉት ተሳትፎ በጣም ትንሽ ነበር፡፡ ምናልባት ፖለቲካ ከውስጤ ወጥቷል ማለታቸውን ተከትሎ በዚህ በኩል ጥያቄ ማቅረብ አይገባ ይሆናል፡፡
ፖለቲካ ከውስጤ ወጥቷል ያሉት ግለሰብ ግን ከበርካታ ወራት መጥፋት በሁዋላ በ2006 ፓርቲውን ለመምራት እንደሚወዳደሩ ተሰማ፡፡ ለኔ በጊዜው ዳግም ለመወዳደር ያቀረቡት ምክንያት አሳማኝ አይደለም ነበር፡፡ በዛን ሰሞን የሚሊዮኞች ድምፅ ለነፃነት እንቅስቃሴ ወቅት በሰላማዊ ሰልፍ ላይ አግኝቻቸው ሰላምታ እየሰጠሁዋቸው ኢ/ር ጠፉ አልኳቸው ምንም ሊመልሱልኝ አልቻሉም፡፡ እስከሚገባኝ አንድ ግለሰብ ፓርቲውን ማገልገል ያለበት በአመራር ደረጃ ብቻ ሁኖ አይመስለኝም፡፡ በተራ አባልነትም ሆኖ አክቲቭ አንቅስቃሴ ማድረግ ይችላል ባይ ነኝ፡፡ ይሄ ስልጣንን እንደ እርስት የማየቱ ነገር ትግሉን ወደ ሁዋላ ከመሳብ ውጪ የሚፈይደው አንዳችም ነገር የለም፡፡
ታህሳስ 2006 ዓ.ም በተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ኢ/ር ግዛቸው ባብላጫ ድምፅ አሸንፈው ዳግም ፓርቲውን መምራት ጀመሩ፡፡ ትዝ ይለኛል ከዚህ ጋር ተያይዞ በፃፍኩት ፅሁፍ ‹ከተተኪ ጋር ተያይዞ የኢንጅነር ግዛቸው ወደ ስልጣን መምጣት ብቻውን በፓርቲው ውስጥ ያለውን ለውጥ የሚሸፍነው አይመስለኝም› ብዬ ነበር፡፡ እውነት ነው፡፡ እነ በላይ ፍቃዱ እነ ሐብታሙ አያሌው እነ እነ ሰለሞን ስዩም እነ ዳንኤል ተፈራ እነ ዳንኤል ሺበሺን የመሰሉ ተስፋ የሚጣልባቸው ግለሰበቦች ወደፊት እየመጡ ነበር፡፡ ይህን በማየት ነበር ባልደግፋቸው እንኳን ያልተቃወምኳቸው፡፡ በተለይ ያዋቀሩት ካቢኔ ከላይ ያቀረብኩትን መከራከሪያ የሚያጠናክርልኝ ነበር፡፡
ሁኔታው በዚህ መንገድ እንደቀጠለ ፖለቲካ ከውስጤ ተሟጦ አልቋል ያሉት ግለሰብ ፓርቲውን መምራት ከጀመሩ ከአስር ወራት በሁዋላ በኢንጅነሩ አካሄድ ያልተደሰቱ የስራ አስፈፃሚ አባላት እራሳችውን ከስራ አስፈፃሚነት በማግለል በፓርቲው አባልነታቸው እንደሚቀጥሉ ተናገሩ፡፡ እዚህ ጋር እኚህ ግለሰቦች ይህን ሲያረጉ የፈጠሩት ምንም አቧራ የለም፡፡ ይህ ለነገ ትምህርት የሚሆን ገንቢ ጅማሮ ነው፡፡ ይህን ያልኩት እንዲሁ ሳይሆን አቧራ መፍጠሩ አልያም ጋዜጠኛ ጠርቶ ማራገቡ ማንን እንደሚጠቅም ጠንቅቀው የሚያውቁ ስልጡን ፖለቲከኞች ናቸውና ነው፡፡ይህን ተከትሎ የተጓደለው ካቢኔያቸውን በሙሙላት ለመቀጠል ቢሞክሩም ብዙም መራመድ አልቻሉም፡፡ በዚህም ምክንያት ካቢኔያቸውን በመበተን ‹‹ከውስጥና ከውጭ በተፈጠሩብኝ ግፊት ስልጣኔን ለማስረከብ ተገድጃለሁ›› ብለው ለብሔራዊ ምክር ቤቱ ስልጣናቸውን አስረከቡ፡፡ ምክር ቤቱም ጥያቄያቸውን በመቀበል በሳቸው ምትክ አወዳድሮ የፓርቲውን መሪ አስመረጠ፡፡
ኢ/ር ግዛቸው ስልጣናቸውን ሲያስረክቡ ያሏት ሌላዋ ነገር ‹‹ፓርቲው እንዳይጎዳ›› የምትል ነገር ነበረች፡፡ ከጥቂት ጊዜ በሁዋላ ፓርቲው መካሪ አልባ በሆኑ ግለሰቦች እና በምርጫ ቦርድ ህልውናውን የሚንድ ተግባር ሲፈፀም ምንም አላሉም፡፡ ምንም ህጋዊ መብት ሳይኖራቸው በየሆቴሉ እየሄዱ ‹‹ኢ/ር ግዛቸው ከስልጣናቸው የወረዱት ህገ ወጥ በሆነ መንገድ ነው›› እያሉ በስማቸው የሚነግዱባቸውን ሰዎች እንኳ በስሜ አትነግዱ ለማለት አልሞከሩም፡፡ ይህ ለኔ አስተዛዛቢ ነው፡፡ ቀደም ሲል ‹‹ፓርቲው እንዳይጎዳ ብዬ ነው›› ሲሉ የነበሩ ግለሰብ ፓርቲው ህልውናውን የሚያሳጣ ዘመቻ ሲከፈትበት ከፓርተው ጎን በመሆን ፋንታ ጭራሽ በዘመቻው በመካፈል በፋና ሬዲዮ ቀርበው ያሉት ለኔ ፍፁም እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል! ካልሆነ በስተቀር አንድ በመሪነት የነበረ፣ የስርዐቱን እኩይ ተግባር ላለፉት አስርታት በቅርብ ያየ ግለሰብ የሚሳሳተው ነው ብዬ ማሰብ ይቸግረኛል፡፡
ይሄ ከላይ ብቻ ተቀምጦ ስልጣንን የሙጥኝ የማለት ሜንታሊቲ የፈጠረው ተፅእኖ በፖለቲካው ውስጥ ቀላል አይደለም፡፡ ለምሳሌ ፕ/ር በየነ እና ዶ/ር መረራ ላለፉት ሁለት አስርታት ከላይ ቁጭ እንዳሉ ናቸው፡፡ አሁን እኚህን ግለሰቦች ለሁለት አስርታት ከተቀመጡበት ወንበር ተነስታችሁ በምክትል ሊቀመንበርነት አልያም በፀሃፊነት አልያም በድርጅት ጉዳይ ስሩ ብትላቸው ሞት እንደሚመስላቸው ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ተተኪ የለም የሚሏት ቧልት የእውነት ተተኪ ሳይኖር ቀርቶ ሳይሆን ከእርስታቸው ላለመላቀቅ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ነው ከታች ወርዶ መስራት ሞት የሚመስላቸወ ቁጥራቸው ጥቂት ያልሆነው፡፡ የሆነው ሆኖ ከታችም በመሆን ፓርቲንም ሆነ አገርንም ማገልገል ይቻላል ባይ ነኝ፡፡ እኔ ብቻ እላይ ካልተሰቀልኩ ማለት የዘመኑን ፖለቲካ ስለማይመጥን ይቅርብን፡፡ እዛው አንድነት ውስጥ ለወጣቶች ቦታቸውን በመልቀቅ በፓርተው እንቅስቃሴቸውን ያላቋረጡ እንደ ዶ/ር ሀይሉ አርአያና አቶ አስራት ጣሴ ያሉ ለሌሎች አርያ ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው፡፡
ወደ ኢ/ር ዘለቀ ስንመጣ እንቅስቃሰውን መታዘብ የጀመርኩት ፓርቲውን ዶ/ር ነጋሶ በሚመሩበት ጊዜ ከመሪው ጋር በተፈጠረ ችግር አቧራ በማስነሳት ዶክተሩን ‹‹አለም ላይ ካሉ ግልፍተኞች ዶ/ር ነጋሲ ቢወዳደሩ ከፊተኞቹ ተርታ እንደሚሰለፉ›› በመናገር ‹‹በቃኝ›› ሲል በሰንደቅ ጋዜጣ ሰፊ ሽፋን እንዳገኘ አስታውሳለሁ፡፡ ይህን ልተገራ ድርጊቱን ሳያርም የዶክተሩን ከፓርቲ ስልጣን መውረድ ተከትሎ ዳግም ወደ ስራ አስፈፃሚነት በመግባት እሱና መሰል መካሪ አልባ ግለሰቦች በመሆን በፓርተው ስም መግለጫ መስጠት ስልጣን ሳይኖራቸው በየሆቴሉ በመሄድ ‹‹መርህ ይከበር›› ሲሉ የ በእርግጥም የሚከበር መርህ ቢኖር እንኳ በፓርቲው ደንብ መሰረት በውስጥ መጨረስ ሲቻል በማን አለብኝነት የሄዱበት መንገድ አስተዛዛቢ ነው፡፡
‹‹መርህ ይከበር›› እያሉ ከሆቴል ሆቴል እየሄዱ መግለጫ በሚሰጡበት ሰሞን ለኢ/ር ዘለቀ በግልፅ ጥያቄዎቼን አቅርቤ ብፅፍለትም ምንም አልመለሰልኝም ነበር፡፡ በጊዜው ከጠየቅኳቸው ጥያቄዎች ውስጥ ይህ ይገኝበታል፡፡ ‹‹ፕሬዝዳንት ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው ከፓርቲ ፕሬዝዳንትነት እንዲነሱ መደረጉ የፓርቲውን ህግ የጣሰ ነው›› ማለታችሁ መሰረቱ ምንድን ነው? ይህንስ እንደ ደና ዜና በቴሌቭዥን መስኮት ቀርቦ ከመናገር ይልቅ ለሚቀርባችሁ እና መልቀቂያውን ለተቀበላቸው ብሔራዊ ምክርቤቱ ማቅረብ አይቻልም ነበር? ስል ጠይቄያቸው ነበር፡፡ እሱ እና መሰሎቹ ግን የያዙት መንገድ ገንቢ አለመሆኑ ቢነገራቸውም አልሰማ በማለት ቀጠሉበት፡፡ከዚህ የምንማረው ነገር በፓርቲ ውስጥ የዲሲፕሊን ችግር ሲፈጠር የማያዳግም እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ነው፡፡ በአንዱ መሪነት ጊዜ ተሳድቦ በሌላው መሪነት ጊዜ መታረሙ ሳይረጋገጥ ዳግም ወደ መሪነት እንዲመጣ መደረጉ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ አንዲህ በቸልታ የሚታለፉ ነገሮች ናቸው የኋላ ኋላ ያየነውን አይነት አደጋ ያደረሱት፡፡
የኢ/ር ዘለቀን ሌጋሲ በመቀበል አቶ ትዕግስቱ ከዳር አድርሶታል፡፡ ስለ አቶ ትዕግስቱ ብዙ ማለት ጉንጭ አልፋ ነው የሚሆነው፡፡ የvoa ጋዜጠኛ የፓርቲውን ህገ ደንብ ቃል በቃል እየጠቀሰ በፓርቲው ውስጥ ልዩነቶች ሲፈጠሩ የሚኬድበትን ቅደም ተከተል እያስቀመጠ ሲጠይቀው መመለስ አቅቶት ‹‹ጥያቄህ አልተመቸኝም፤ ተልዕኮ አለህ ወይ?›› ብሎ መመለሱን ስናስተውል፡፡ ‹‹መርህ ይከበር›› ያሉት ሰዎች የፓርቲው ህግ ምን እንደሚል እንኳ የማያውቁ እንደሆኑ እንረዳለን፡፡ መቼም አቶ ትዕግሰቱ እራሱን ለውርደት አዘጋጅቶ በችሮታ ያገኘውን ስልጣን እስከመቼ ይዞት እንደሚቆይ አይታወቅም፡፡ በእርግጥ ፅ/ቤቱን ይታቀፍ እንደሆነ አንጂ ከዛ የጎላ ሚና አይኖረውም፡፡ ሞተር የሌለው መኪና ታውቃላችሁ አይደል? በቃ አቶ ትግስቱ እንደዛ ነው፡፡ ሞተሩ የወለቀበትን አንድነት ይዞ ወዴትም መራመድ አይችልም፡፡ ይህ ግለሰብ የኢ/ር ግዛቸው ከስልጣን መልቀቅን ተከትሎ ፓርቲውን ለመምራት ከአቶ በላይ ፍቃዱ ጋር ተወዳድሮ ያገኘው አንድ ድምፅ ብቻ ነው፡፡ እሷም አርሱ ለራሱ የሰጣት አንድ ድምፅ፡፡ ይህን ጊዜ ነበር አቶ ትዕግስቱ አካሄዱን ቆም ብሎ መመርመር የነበረበት፡፡ አሁን እሱን ጨምሮ አስር የማይሞሉ ከራሳቸው ተሻግረው ማሰበብ ያልቻሉ መካሪ አልባ ፖለቲከኞችን ይዞ ህጋዊ ነኝ የሚለው፡፡ ሞተር ለሌለው መኪና ከዚህ በላይ ማለት ይበዛልና ትቼዋለሁ፡፡
ይህ መንገድ ግን ትክክል እንዳልሆነ እስከሚገባቸው ድረስ ደጋግመን ልንነግራቸው ይገባል፡፡ መፍጠር በምንችለው ያህል በግለሰቦቹ ላይ ተፅዕኖ ማሳደር አለብን፡፡ በዚህ በኩል ህጋዊው አንድነት ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት መውሰዱ የሚደገፍ ነው፡፡ አሁን ላይ የሰሩትን ነውረኛ ድርጊት ዝም ካልን፤ በዚህ መንገድ በመጓዝ ከተራ አባልነት ተነስተው የፓርቲ ሊቀመንበር ፣ምክትል ሊቀመንበር፣የድርጅት ጉዳይ… የፓርላማ እጩ ከዛም ይህን አስቀያሚ ተግባራቸውን ይዘው ፓርላማ የሚገቡበት መንገድ በገዢዎች ተመቻችቶ ለአምስት አመታት የተከበሩ አቶ እከሌ እየተባሉ የሚቀጥሉ ከሆነ የተቃውሞ ጎራው ከእንዲህ አይነት አይን ያወጣ ሰርጎ ገብነት የሚላቀቅበትን መንገድ አስቸጋሪ ያደረገዋል፡፡ ትግሉንም ካንሰራራበት በመነሳት በእግሩ መሄድ ሲጀምር አንካሳ በማድረግ እዛው አንዲረግጥ ያስገድደዋል፡፡ የዚህ ተግባር ክፉነት ባጠቃላይ በተቃውሞ ጎራው ላይ ስለሆነ ሊታሰብበት ይገባል፡፡
በቅርቡ መኢአድን ዳግም አንዲመሩ ከምርጫ ቦርድ ችሮታ የተሰጣቸው አቶ አበባው መሐሪ ከሐምሌ 14 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ መኢአድን በእሰጣገባ ውስጥም ቢሆን እየመሩ እንደቆዩ ይታወቃል፡፡ በእርግጥ ይህ ችግር ቀደም ብሎ የጀመረ ቢሆንም በእርሳቸው የስልጣን የመጨረሻ ጊዜ ችግሮቹ በመፈታት መስመራቸውን የያዙ መስለው ነበር፡፡ አቶ አበባው እንደ ኢ/ር ግዛቸው ሁሉ ጥቅምት 20 2007 ዓ.ም በፃፉት እና ለጠቅላላ ጉባዔው በንባብ ባሰሙት የሰልጣን መልቀቂያ ስልጣናቸውን እንደሚለቁ አሳውቀዋል፡፡ ጠቅላላ ጉባኤውም ይህን ተቀብሎ በሳቸው ምትክ አቶ ማሙሸትን መረጠ፡፡ አቶ አባበው በአንድ ገፅ በፃፉት የመልቀቂያ ፅሁፍ መጨረሻ አካባቢ እንዲህ የምትል ፅሁፍ ትገኛለች፡፡ ‹‹…የተጣለብኝን ኃላፊነት በመልቀቅ በፓርቲው ውስጥ በተራ አባልነት ለመቀጠል ወስኛለሁ›› ይላል፡፡
አቶ አበባው ግን ያደረጉት ጠቅላላ ጉባኤው እንዳለቀ የፓርቲውን ማህተም እንደያዙ በመሄድ ‹‹በተራ አባልነት ለመቀጠል ወስኛለሁ›› ያሉ ሰውዬ በሌላ አጀንዳ ‹‹የፓርቲው ህግ ተጥሷል በሚል ብቅ አሉ፡፡ ይህ የሚያሳየን ምንድን ነው? አቶ አበባው በተራ አባልነት ለመቀጠል ወስኛለሁ ማለታቸው ከወረቀት የዘለለ ፍላጎት እንዳልሆነ ነው፡፡ ምናልባት የጠቅላላ ጉባኤ አባላት እግሬ ላይ ወድቀው ምራኝ ይሉኛል ብለው ጠብቀውም ይሆናል፡፡ እንዳሉት ስልጣናቸውን ብቻም ሳይሆን ማህተማቸውን አስረክበው የእውነት በተራ አባልነት ቀጥለው ቢሆነብ ኖሮ ትልቅነት ነበር፡፡ በተለይም የአቶ ማሙሸት አማረ ቡድን ከቀድሞው የኢ/ር ሃይሉ ሻወል ሰዎች ጋር እርቅ እንደፈፀሙ ተሰምቶ ነበር፡፡ ምን ይሄ ብቻ በምርጫው ዙሪያ አቶ ማሙሸት አማረ ከሚሊዮኖች ድምፅ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በተለይ እጩዎችን በማቅረብ ደረጃ ትግሉን በሚጠቅም መንገድ በመደጋገፍ እንደሚያቀርቡ ገልፀው ነበር፡፡ ምን ዋጋ አለው ከእራሳቸው አሻግራው በማያዩ መካሪ አልባ ፖለቲከኞች ይህ ሁሉ ባዶ ሆኖ መኢአድ ዳግም ወደ ቀድሞው እንዲመለስ ተገደደ፡፡ በርግጥም መካሪ አልባ ፖለቲከኞች…
ተቃውሞ ጎራው ነገን!
እስካሁን እንዳየነው የተቃውሞ ጎራው መካሪ አልባ በሆኑ የፓርቲ አመራሮች ትግሉ የሁዋሊት ሲጓዝ ቆይቷል፡፡ በዚህ ሂደትም ተካፋይ የሆኑ ሰዎች እያወቁም ሆነ ሳያወቁ ለስርዐቱ መጠቀሚያ ሆነዋል፡፡ እስከሚገባኝ ከራሱ ተሻግሮ ማሰብ የማይችል ግለሰብ ወደ ፖለቲካው ባይመጣ ይመረጣል፡፡ በብዙሃን ድምፅ ለመገዛት ፍቃደኛ የማይሆንም እንደዛው፡፡ ከዛ በተረፈ ግን በፓርቲዎች ውስጥ የውስጥ ትግል መካሄድ የለበትም አልልም፡፡ መካሄድ አለበት፡፡ ሲካሄድ ግን እንዴት ነው? ትግሉን ወደ ኋላ የሚጎትት ሳይሆን ወደ ፊት በሚያራምድ መንገድ መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም በየትኛውም መንገድ ቢሆን መቅደም ያለበት የግለሰቦች ጥቅም ሳይሆን ትግሉ ስለሆነ፡፡ ችግሮች ሲፈጠሩም የትኛውንም ያህል እርቀት ቢሆን ተሂዶ በፓርቲ ጥላ ሰር መፍታት ግድ ይላል፡፡
ጥሩውን ተመኘሁ

No comments:
Post a Comment