Tuesday, 23 August 2016

ስር ነቀል ለውጥ!



ባለፈው ፖለቲካችን በተለይም የስልሳቹ ትውልድ በፖለቲካው በኩል ያደረገው ትግል እንዲሁም የተገኘውን ውጤት ስናይ ከተከፈለው መስዋትነት ጋር ፈፅሞ ሊገናኝ የማይችል ሆኖ እኛገኘዋለን፡፡ በተለይም ትግሉ ጠያቄ የሆኑ ወጣቶቻችንን ቅርጥፍ አድርጎ በመብላቱ አሁን ላይ አደባባዩ ላይ እውቀት ሳይሆን ድፍረት ያላቸው ሆድ አደሮች ቦታውን እንዲፈነጩበት ሆኗል፡፡ ይህም ለውጡን ስር ነቀል ከማድርግ ይልቅ አንዱን አምባገነን በሌላው በመተካት በሳዛኝ ሁኔታ ተጠናቋል፡፡



ደርግ ወርዶ ዘመነኞቹ ከፋፋይና አምባገነን መሪዎች ስልጣን ከተቆጣጠሩ ጀምሮ እንዳለፈው አቻቸው በግልፅ በቴሌቭዢን መስኮት ቀርበው ‹‹ለምሳ ያሰቡንን ለቁርስ አረግናቸው›› አይበሉን እንጂ መግደሉና ማሰሩ የእለት ተለት ተግባራቸው ነው፡፡ በተለም በአገሪቱ ውስጥ ለሚነሱ የመብት ጥያቄዎች እስካሁን ድረስ ከጠብ-መንጃ የተሻለ መልስ አልሰጡም፡፡ ዛሬም ኢትዮጵያውያን ለሚያነሱት የመብት ጥያቄዎች መልሱ የጅምላ እስር፣ ሞትና ስደት ሆኗል፡፡



አሁንም ቢሆን ለውጥ ወዳድ የሆኑ ግለሰቦች የሚሄዱበትን መንገድ ደግመው ደጋግመው ሊፈትሹ ይገባል፡፡ ቤት ለቤት የደረሰውን የስርዐቱን  አፈና እንዲሁ በአንድ ለሊት አሸንፎ መውጣት ይቻላል የሚል ቅዠት ውስጥ በፍፁም ሊገቡ አይገባም፡፡ ምክንያቱም ትግሉ የሚካሄደው ከገዢዎች ጋር ብቻ አይደለምና፡፡ እንዲሁም የሚከፈለው መስዋትነት እንዳለፈው አንዱን ጨቋኝ በሌላው ጨቋኝ መተካት ሳይሆን  ፖለቲካውን ከጉልተኛውና ከደብተራው ባህል አላቆ፣ ከሆዳምነትና ከግላዊ የከንቱነት ስሜቶች፣ ከእብሪት እና ከማን አንሼ ባይነት አፅድቶ በምክንይት ላይ የቆመ የነፃነት፣ የብልፅግና፣የእውቀት፣የእኩልነት እና የፍትህ መሳሪያ በማድረግ ማዘመን ነው፡፡



ይህንን ደግሞ ገዢዎቻችን በቀደዱልን መንገድ ተጉዘን እንሞክረው ብንል  እዛው ከመርገጥ ውጭ ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት አይቻለንም፡፡ መሆን ያለበት የገዢዎችን የከፋፍለህ ግዛ አጥር ሰብረን በመውጣት መሰረታችንን ሰብአዊነት ላይ በማድረግ በአንድነት መነሳት ይኖርብናል፡፡ ካለበለዚያ ገዢዎቻችን በቀደዱልን ፈሰን ለየብቻ የምንጮህ ከሆነ እራሳችንን ለገዢዎቻችን በትር እንዲመች አድርገን  አዘጋጅተናል  ማለት ነው፡፡ ስለሆነም የመብት ጥያቄዎች ይህ አካል ወይም የዚህ ቋንቋ ተናጋሪ ስላነሳቸው ሳይሆን  መሰረቱ ጥያቄው ነው መሆን ያለበት፡፡

የስርዐቱ ኢ-ፍትሃዊ እና  አደህይቶ መግዛት በመላ አገሪቱ እየተተገበረ ያለ  ነው፡፡ ለምሳሌ በጋምቤላ ሰፋፊ መሪቶችን ለውጭ አገር ባላሃብቶች እየሰጡ  በሰፈራ ስም ነባሩን ገበሬ ከሰፋፊ ቦታዎቹ እያፈናቀሉ አንድና ሁለት ከብት እንኳ ማኖር በማያስችል ጠባብ መሬት እንዲቀመጥ ያስገድዱታል፡፡ በጉራፈርዳ የሚኖሩ የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ላይ አገራችሁ አይደለም ተብለው ያፈሩት ንብረት ተዘርፎ፣የተወሰኑት ተገድለው የተቀሩት ባዶ እጃቸውን ወጥተዋል፡፡ አሁን ተማሪዎች ተቃውሞ እያሰሙ ያሉትም በኦሮሚያ ልዩ ዞን ያሉ ቦታዎችን ወደ አዲስ አበባ ማካለል በሚል አንዱን በማደህየት ሌላውን ማደለብ ነው፡፡ የስርዐቱን ኢ-ፍትሃዊ ድርጊት  እንዲህ እንዲህ እያልን ብዙ መጥቀስ እንችላለን…




መረሳት የሌለበት ይህ ስርዐት እስካለ ድርስ ዜጎችን ማፈናቀልና አደህይቶ መግዛት ይቀጥላል፡፡ አሁን ተቃውሞ እየቀረበበት ካለው ማስተር ፕላን  ጥንስስ በፊት በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ሰፋፊ መሪቶች እንደጉድ ተቸብችበዋል፡፡ ነዋሪዎቹ ተፈናቅለው  ለቦታቸው ምትክ በሚል የሚሰጧቸው ገንዘቦች ከፋፋዮቹ ገዢዎችና የእነሱ የጥቅም ፓርትነሮች ከሚያገኟቸው አንፃር ሲታይ የብላሽ አይነት ነው፡፡ ስለሆነም ስርአቱ እስካለ ድርስ እስሩ፣ስደቱ ሞት እና  እና ኢ-ፍትሃዊ ድርጊት ይቀጥላል፡፡ የለውጡ ዋና አላማም በየትኛውን ብዱን ላይ መነሳት አልያም ጥላቻ ሳይሆን በመሰረታዊነት ከአገዛዝ ቀምበር በመውጣት ወደ ዲሞክራሲ የሚያስኬደውን ይህም ሁላችንንም በጋራና በእኩልነት ወደሚያስተዳድር ስርዐት ማምራት ነው፡፡



ይህም ጉዞ የተሳካ የሚሆነው የተወሰነ አካል አልያም ቡድን  ሞቶ ሌላውን ነፃ ለማውጣት ሳይሆን እያንዳንዱ  ዜጋ ገዢዎቹ ያነበሩበትን ጭቆና አራግፎ በመጣል እራሱን የለውጡ አካል በማድረግ የበኩሉን ሲያደርግ ነው፡፡ ይህም ከለውጡ በኋላ ስርነቀል ለውጡ እንዳይቀለበስና የባለቤትነት ስሜት ተሰምቶት በንቃት እንዲጠብቅ ያስገድደዋል፡፡ ሁሉም ግዴታ የድርጅት አባል ይሁን ባይባልም ባለበትና በተሰማራበት ቦታ ሁሉ የገዢዎችን የጭቆና ቀንበር አራግፎ  በመጣል ትግሉ  በዋነኝነት ተቋማዊ መሰረት አንዲይዝ መታገል አለበት፡፡ በእርግጥም የትውልዱም ሆነ የለውጥ ወዳዱ ዜጋ ዋነኛ ጭንቀት ስርአቱን ከስልጣን ማውረድ አይመስለኝም ምክንያቱም ስርቱ የትጋት ጊዜውን ጨርሶ የልግመት ጊዜ ላይ ነውና! መውረዱ የማይቀር ነው፡፡ ዋነኛው  ጉዳይ ከአገዛዝ ወደ አገዛዝ ሳይሆን ካገዛዝ ወደ ዲሞክራሲ ነውና!
ጉዞ ወደ ፊት!

No comments:

Post a Comment