Tuesday, 23 August 2016

የስርዐቱ የይቅርታ ካርድ እየመሸበት ይሆን?



ስርዐቱ ከምርጫ 97 በኋላ በተለይም የፖለቲካ አመራሮችን፣ጋዜጠኞችን በአመለካከታቸው ከስርዐቱ በተቃርኖ ስለቆሙ ብቻ ወደ ማጎሪያዎቹ የሚያስገባቸውን ንፁሃን ባላጠፉት ጥፋት ከሶ የፍርድ ውሳኔ ካስተላለፈባቸው በኋላ በውስጥም በውጭም  ግፊት  ሲበረታበት ለፖለቲካ ትርፉ ሲል የይቅርታ ካርድ ይመዝና ከእስር ያስወጣቸዋል፡፡ ለዚህም በቅንጅት አመራሮች እንዲሁም በብርቱዋ የፖለቲካ መሪ ወ/ሪት ብርትኳን  ሚደቅሳ የሆነው ለዚህ ሁነኛ ማሳያ ማሳያ ነው፡፡



 እቺ ‹‹ይቅርታ›› የሚሏት  የመጫወቻ ካርድ በገዢዎቹ አተረጓጎም የስሟን እሩብ እንኳን የማትመዝን በተለይም ታሳሪዎቹ ከእስር ከተለቀቁ በኋላ ዳግም ወደቀድሞ እንቅስቃሴያቸው ቢገቡ እንደማስጠንቀቂያ  እቺው የይቅርታ ካርድ ተመዛ ወደ እስር እንደሚወረወሩ ማስፈራሪያም ጭምር ናት፡፡ ሌላው በምርጫ ዘጠና ሰባት እንደታየው ስርዐቱ ኮሮጆ ገልብጦ ተቃውሞ ሲበረታበት የቅንጅት አመራሮችንና ጋዜጠኞችን ጠራርጎ አስሮ የህዝብን ጥያቄ ከድምፃችን ይከበር ወደ መሪዎቻችን ይፈቱ ዳይቨርት በማድረግ በመጨረሻም በአቶ በረከት አገላላፅ ከናዳው ለማምለጥ እስርና እቺኑ የይቅርታ ካርድ ተጠቅሟል፡፡  በቀጣይ ጊዜም እቺኑ ካርድ  በተመሳሳይ መንገድ ለፖለቲካ መሪዎች እንዲሁም ለጋዜጠኞች እንዲሁም ለሓይማኖት መሪዎች ጭምር ለመጠቀም ተሞክሯል፡፡



ይህ ሁኔታ በጋዜጠኛና መምህርት ርዕዮት አለሙን በተመሳሳይ መንገድ ከእስር እንድትወጣ የተደረገው ውትወታና በእስር ቤት  ይደርስባት የነበረውን  ተፅእኖን ተቋቁማ ባላጠፋችው ጥፋት ይቅርታ እንደማትጠይቅ  አስረግጣ በመንገር የስርዐቱን ሴራ በማክሸፍ የእስር ጊዜዋን ጨርሳ ወጥታለች፡፡ ከዚህ ጊዜ በኋላ የስርዐቱ የይስሙላ የይቅርታ  ካርድ  እየመሸባት ስለመሆኑ ሌላው ማሳያ የሙስሊሙ ህብረተሰብ ጥያቄ ነው፡፡



ስርዐቱ ህዝበ ሙስሊሙ ከመረጣቸው የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ጋር ሲነጋገር ቆይቶ ጥያቄው እየሰፋ ሄዶ በክልል ያለውን ህዝበ ሙስሊም ማነቃነቅ ሲጀምር  የኮሚቴው አባላትን  በማሰር ጥያቄውን ዳይቨርት ለማድረግ  ቢሞከርም እንዲሁም የኮሚቴው አባላት በተመሳሳይ የይቅርታ ካርድ ተመዞ ከእስር እንዲፈቱ ቢጠየቁም ፈቃደኛ ሳሆኑ ቀርተዋል፡፡ የሙስሊሙ ድምፃችን ይሰማ  እንቅስቃሴ መሪዎቻችን ይፈቱ የሚለውን ጥያቄ ለይቶ ከማስተጋባት ይልቅ ቀድሞ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ከጠየቃቸው ሶስት ጥያቄዎች በመቀጠል አራተኛ አድርጎ በመጠየቅ አሁን ካለበት ደርሷል፡፡

 
የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን እና የጦማሪኑን እስር ተከትሎ ለማሳያነት  የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን የተወሰኑም ቢሆን ክሳቸው ተቋርጦ በነፃ ሲሰናበቱ ሌሎች በውጭ በመሆን ጉዳያቸው እየታየ ነው፡፡  በቅርቡም የአንድነትና የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች  ጊዜያቸውን ጨርሰው ከእስር ሲፈቱ፤ የአረና ፓርቲው አብርሃ ደስታ ከወራቶች በሁዋላ የእስር ጊዜውን ጨርሶ ከእስር አንደሚወጣ ታውቋል፡፡ በእርግጥ አሁን ላይ ሁኖ የስርዐቱ የይቅርታ ካርድ መሽቶበታል  ብሎ መደምደም አይቻል ይሆናል፡፡ ይህ በተለይም በተቃውሞ ጎራው ውስጥ  ያሉ አባላትና አመራሮች ሲታሰሩ እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ፓርቲ እንዲሁም በአገሪቱ ባጠቃላይ የፍትህና የዲሞክራሲ ጥያቄዎችን ተከትሎ ለሚመጡ የገዢዎች ጅምላ እስር የሚሰጠው ግብረመልስ ወሳኝነት ይኖረዋል፡፡
01/09/08

No comments:

Post a Comment