ደጋግመን እንደምንሰማው ሰላም ማለት የጥይት ድምፅ አለመሰማት እስኪመስል ድረስ ተደጋግሞ ሰላም፣ሰላም ይባላል፡፡ በዚህ
መሃል ንፁኃኑ ሃሰባቸውን በመግፃቸው ብቻ ወደ ማጎሪያዎቹ ይወረወራሉ፡፡
የሃይማኖት ነፃነት ጥያቄ ያነሱ ዜጎች የሽብር ታርጋ እየተለጠፈባቸው ይታሰራሉ፡፡ ፖለቲከኞች ከስርዐቱ በተቃርኖ በመቆማቸው ብቻ
ይታሰራሉ፣ይንገላታሉ፣ይገደላሉ፣ይሰደዳሉ፡፡ መንግስትን ለመቃወም አደባባይ የሚወጡ ንፁሃን ዜጎች የጥይት እራት ይሆናሉ፡፡ ይህን
ተከትሎ ከመንግስት ባለስልጣን እስከ ተራው ዜጋ ስለ ሰላም ያወራሉ፡፡ ልማታችንን ለማስቀጠልና ለማፋጠን ሰላም ወሳኝ ነው ይሉሃል፡፡
የቤተ እምነት ሰዎችም ይከተሉና ተመሳሳይ ነገር ይናገራሉ፡፡ በተመሳሳይ ጎንህ ጋር ያለውም ሰላም እፈልጋለሁ ይልሃል፡፡ እዚህ ጋር ሰላም፣ ሰላም እየተባለ እዚያ ጋር ንፁሃኑ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው ይታያሉ
እና ሰላም ምንድን ነው? የሚለው ጭንቅላቴን እያዞረው ከዚህ በታች ያለውን የፕሮፍ መስፍን ፅሁፍ አገኘሁ፤ እንደወረደ አቅርቤዋለሁ፡
ለብዙ ሰዎች ሰላም ማለት ጦርነት የሌለበት ሁኔታ ነው፡፡ ወገን ወይም ቡድን ለይተው ጦር መሳሪያ መዝዘው ካልተዳሙ፣ካልተቆሳሰሉና
ካልተገዳደሉ ሰላም ነው ይባላል፡፡ ይህ ሁኔታ የሰላም ሁኔታ ላይሆን ይችላል፡፡ አንድ አባት ልጁን በጥፊ ወይም በለበቅ እየደበደበ
‹‹ጭጭ፣እስቲ ትንፍሽ!›› እያለ ማልቀስ እንኳን ቢከለክለው፣ ወይም አንድ ሰው አንድ ሌላ ሰው ደረት ላይ ቆሞ ትንፋሽ ቢያሳጣው፣አንድ
ህዝብ በፖሊስና በጦር ሃይል ተሰንጎ ተይዞ ጭጭ ብሎ በደሉንና ጥቃቱን ቢችል ሰላም ነው ማለት አይደለም፡፡ኃይለኛ ደካማውን ሲያጠቃ
ሰላም የለም፤ብዙዎች ጥቂቶችን ሲያጠቁ ሰላም የለም፤ጥቂቶች ተደራጅተውና ታጥቀው ብዙዎችን ሲያጠቁ ሰላም የለም፡፡ ጸጥ፣ለጥ ብሎ
መገዛት ሰላም አይደልም፡፡
ጦርነት ባለመኖሩ ብቻ ሰላም አለ ማለት አይቻልም፡፡ ኃይለኞች ደካሞችን አስገብረው፣በጉልበታቸው የሰውን ልጅ መንፈስ
ገድለው፣አእምሮው ታዛዥና ተገዢ ብቻ እንዲሆን አድርገው በድኑን አንደአሻንጉሊት በሚጫወቱበት ሁኔታ ሰላም የለም፡፡ እንኳን መሳሪያ
አንስቶ ለመዋጋት መረረኝ፣ደከመኝ ለማለት የሰው ልጅ የመንፈስ ሃይሉ ተሟጦ በድን፣ የቁም ሬሳ ሆኖ በሚንገላታበት የአገዛዝ ስርዐት
ውስጥ ሰላም የለም፡፡ በእንደዚህ አይነቱ ሁኔታ ውስጥ ጥላቻ፣ወፍራምና ልብን ሞልቶ የታፈነ ጥላቻ አለ፡፡ጥላቻ ክፉ ጦርነት ነው፡፡
የተጠቃ፣የተበደለ፣የተበዘበዘና የሰውነት ክብሩን የተገፈፈ ሰው በልቡ ውስጥ የታመቀው ጥላቻ እያደገ ጊዜና ሁኔታው ሲፈቅድለት ግፈኞችን
ይዋጋል፡፡ ስለዚህ ግልጽና ገሃድ አይሁን እንጂ ጦርነት አለ፡፡ ከጥላቻና ከሚመግል ቂም የሚመነጨው የደካማዎች ጦርነት በይበልጥና
በተጨማሪ ራስን በመጉዳት የሚደረግ ጦርነት ነው፡፡ ጊዜ ይፈጃል እንጂ ምንጊዜም ድል የደካማዎቹ ብዙኃን ነው፡፡
እንግዲህ ሰላም አፋዊ ጸጥታ ብቻ አይደለም ማለት ነው፡፡ ሰላም የውስጥና የመንፈስ ደስታና እርካታም ነው፡፡ ሰላም ለራስና
ለሌሎች ሰዎች ሙሉ አክብሮት ሲኖር ነው፡፡ ሰላም በራስና በሌሎችም ሰዎች መካከልመተማመን ሲኖር ነው፡፡ ሰላም በአለው ህግና ስነ
ስርዓት ላይ ሙሉ እምነት ሲኖርና በበጎ መንፈስ የራስን ችሎታ በማዳበር የግል ኑሮን ለመምራት የሚያበቃ ሁኔታ ሲኖር ነው፡፡ በአገራችን
ብዙ ሰዎች የማይገነዘቡት ሌላ ነገር አለ፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ለጦርነት የሚከፈለውን ያህል ለሰላምም ይከፈላል፡፡ በሌላ አነጋገር
ጦርነትን በነፃ ያለምንም ክፍያ ማካሄድ እንደማይቻል ሁሉ ሰላምንም ያለምንም ክፍያ በነፃ የሚያገኝ ህዝብ ወይም ኅብረተሰብ የለም፡፡
ለሰላም የሚከፈል ዋጋ አለ፡፡ ሰብአዊ መንፈስንና ሰብአዊ ክብርን
ጠመንጃ ላነገተ ሁሉ ባለመገበርና አሻፈረኝ በማለት የሚከፈል ዋጋ አለ፡፡ የራስንና የሌሎችን መብት ለማክበርና ለማስከበር የሚደረገው
ጥረት ዋጋን ያስከፍላል፡፡
ለሰብአዊ ክብር፣ለእኩልነትና ለፍትህ፣ለነፃነትና ለመብት፣በአጠቃላይም ለሙሉ ሰላም ለሚደረገው ትግል ጨቋኞችም ተጨቋኞችም
ተገቢውን ዋጋ ይከፍላሉ፡፡ የጭቆና ቀንበርን የተሸከሙት እንቢኝ አሻፈረኝ ብለው የእምቢተኛነታቸውን ዋጋ ሳይከፍሉ ከጭቆና አይገላገሉም፡፡
ጨቋኞችም በሰው ልጅ የመንፈስ ኃይል ተሸንፈው የጭቆና መሳሪያቸውን ካላጡ በጭቆና ላይ ከተመሰረተው የበላይነታቸው አይገላገሉም፡፡
ይህም ማለት በጨቋኝና በተጨቋኝ መሀከል ሰላም የሚሰፍነውና ጭቆና የሚጠፋው ጨቋኙ ዝቅ ብሎ ተጨቋኙ ከፍ ብሎ ሁለቱም በሰውነት ደረጃና
በህግ ፊት እኩል ሆነው ሲቆሙ ብቻ ነው፡፡ ጭቆናና የጭቆና መሳሪ እስካለ ድረስ ሰላም አይኖርም፡፡
ምንጭ; ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም 1986 ኢትዮጵያ -ከየት ወዴት? ገፅ 81-82
No comments:
Post a Comment